“በመንፈቀ ሌሊት ግን ጳውሎስና ሲላስ እየጸለዩ እግዚአብሔርን በዜማ ያመሰግኑ ነበር፥ እስረኞቹም ያደምጡአቸው ነበር።
ድንገትም የወኅኒው መሠረት እስኪናወጥ ድረስ ታላቅ የምድር መንቀጥቀጥ ሆነ፤
በዚያን ጊዜም ደጆቹ ሁሉ ተከፈቱ የሁሉም እስራት ተፈታ” (ሐ.ሥ. 16፥25-26)
በጨለመብን ነገር ሁሉ እግዚአብሔር ጣልቃ ሲገባ እንዲህ ይሆናል። ለመርዶክዮስ ብሎም ለእስራኤል የተዘጋጀውን የሞት ድግስ አዋጅ ንጉሡን እንቅልፍ ነሥቶ የገለበጠ አምላክ ስለ እያንዳንዳችንም ጉዳይ ግድ ይለዋል። በዚህ ቃል ማስተዋል
ያለብን ሁለት ነገሮች አሉ። 1ኛው ጊዜው ነው፣ “መንፈቀ ሌሊት” – እጅግ የጨለመበት ሰዓት። ይህም ጨለማውን የሚያስወግድ የእግዚአብሔር ማዳን ከመምጣቱ በፊት አሁን ካሉበት ይልቅ ሁኔታዎች ሊከፉ ወይም ሊብሱ እንደሚችሉ
ያሳያል። 2ኛው እጅግ ቢጨልም፣ እጅግ ቢከፋም ጳውሎስና ሲላስ – መጸለቸው፣ እግዚአብሔርን በዜማ ማመስገናቸው ነው። በብዙ ድብደባ ካባበጡ ከንፈሮች መሃል፣ ከቁስል ውስጥ፣ ከመከራ ጀርባ ምስጋና ሲወጣ ምድርን የሚያንቀጠቅጥ፣
የውህኒ ቤቱን መሠረትንም የሚያናውጥ የእግዚአብሔር ማዳን ተአምራት ሆነ። ውጤቱም፦ ደጆቹ ሁሉ ተከፈቱ፣ የሁሉም እሥራት ተፈታ! የወኅኒ ቤቱ ጠባቂና ቤተ ሰቦቹም የዘላለም ሕይወት እዳሎት ተካፋይ ሆኑ፣ ይገርማል! እግዚአብሔር
በቍስል አልፎ ሌሎችን ሲፈውስ! እግዚአብሔር በጨለማችን አልፎ ለኛም ሆነ ለሌሎች የብርሃን ወጋገን ሲፈነጥቅ! ይገርማል! የእግዚአብሔር ማዳን የተገለጸበት ጎዳና ልብ ይበሉ! ምስጋና! ጌታ ራሱ “ምስጋና የሚሠዋ ያከብረኛል
የእግዚአብሔርን ማዳን ለእርሱ የማሳይበት መንገድ ከዚያ አለ” (መዝ. 50፥23) ብሏልና። ከመከራ ውስጥ የሚፍለቀለቅ ምስጋና – ተአምራትን የሚስብ ማግኔት!
መዝሙር
አቤቱ እናመሰግንሃለን (2)
ስምህንም እንጠራለን (2)
- ከፍ ከፍ አርገን አንተን አክብረን
ታላቅ ስምህን ደጋግመን ጠርተን
የዝማሬያችን መሥዋዕት ወጥቶ
ታከብረዋለህ ልክ እንደ ሽቶ፣
አቤቱ እናመሰግንሃለን . . .
- የሚሰዋልኝ ለእኔ ምስጋና
እርሱ ያከብረኛል ብለሃልና
እኛም ወደናል ለማክበር አንተን
ከሁሉም በላይ ክበር ተመስገን፣
አቤቱ እናመሰግንሃለን . . .
- አንተ ከፍ በል ጠላት ተዋርዶ
እኛም እንስገድ በረከት በረከት ወርዶ
ካላንተ ለእኛ ማን አለንና
በሙሉ ኃይላችን ይኸው ምሥጋና፣
አቤቱ እናመሰግንሃለን . . .
- ከስሞች በላይ ታላቅ ስም ይዘህ
በሰማይ ስፍራ በክብር ያለህ
አንተ ነህና ለኛ ተስፋችን
ስምህ ሲጠራ ስማን ጌታችን፣
አቤቱ እናመሰግንሃለን . . .
- ብለን ስንጮህ አቤቱ አቤቱ
ፈጥነህ የምትሰማን ኃያል ነህ ብርቱ
ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም
በእልልታ ሆታ ክበር ተመስገን፣
አቤቱ እናመሰግንሃለን . . .