“ኢየሱስም በቢታንያ በለምጻሙ በስምዖን ቤት ሳለ፥ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ የበዛ ሽቱ የሞላው የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ይዛ ወደ እርሱ ቀረበች በማዕድም ተቀምጦ ሳለ በራሱ ላይ አፈሰሰችው። ደቀ መዛሙርቱም ይህን አይተው ተቈጡና። ይህ ጥፋት ለምንድር ነው? ይህ በብዙ ዋጋ ተሽጦ ለድሆች ሊሰጥ ይቻል ነበርና አሉ። ኢየሱስም ይህን አውቆ እንዲህ አላቸው፦ መልካም ሥራ ሠርታልኛለችና ሴቲቱንስ ስለ ምን ታደክሙአታላችሁ? . . . . እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ወንጌል በዓለም ሁሉ በማናቸውም ስፍራ በሚሰበክበት እርስዋ ያደረገችው ደግሞ ለእርስዋ መታሰቢያ እንዲሆን ይነገራል”(ማር. 14፥1፤ ማቴ. 26፤ ዮሐ. 12)
ጌታ ኢየሱስ ሊሰቀል ሳምንት ሲቀረው በቢታንያ በለምጻሙ በስምኦን ቤት አንድ ታሪክ ተፈጸመ። ጌታ ኢየሱስ ወደ ስምኦን ቤት እራት ተጋበዘ። ቢታንያ በኢየሩሳሌም አካባቢ በደብረ ዘይት ምስራቃዊ ክፍል የምትገኝ ትንሽ ከተማ ናት። አልዓዛር፣ ማርያምና ማርታ በዚያ ተገኝቷል። ይህ ወንጌል ሲሰበክ የእርሷ ታሪክ አብሮ እንዲነገር አዘዘ።
ጌታ ከዚህስ ምን ሊያስተምረን ፈልጎ ነው? 1. “የመፍሰስ” 2. “የመባከን” 3. “የመሰበር” 4. “የመጥፋት” 5. “በእግሩ ሥር የመቆየት” ፕሪንስፕል የምንማርበት ክፍል ነው። በመጀመሪያ “መባከን” ምን ማለት ነው? ገንዘብን፣ ንብረትን፣ ጊዜን ሕይወትን ከታቀደለትና ከሚፈለገው በላይ ማጥፋት። ሰዎች ወንጌልን ሰምተው ወደ ጌታ እንዲመጡ፣ በእርሱ አምነው እንዲድኑ፣ የዘላለም ሕይወት እንዲወርሱ፣ ከሞት ወደ ሕይወት እንዲሻገሩ የምስራቹ ቃል ይሰበካል። ይህም የማርያም ፕሪንስፕል አብሮ ይሰበካል። ዛሬ ስለ አገልግሎት፣ ስለ ቅባት፣ ስለ ልዩ ልዩ ነገሮች እንጸያለን። ነገር ግን የማርያምን ፕሪንስፕል ከወንጌል አገልግሎት ጋር ልንቀበለው ያስፈልጋል።
• ብልቃጡ (እኛነታችን) እስካልተሰበረ ድረስ ለብዙዎች አንደርስም።
• ያለንን ውድ ነገር (ጊዜ ፣ ገንዘብ ፣ . . .) በጌታ እግር ሥር አፍስሱ፣ ከዚያም ሽቶው ያውዳል፣ መዓዛው ይወጣልሌሎችም ያሸቱታትል።
• የወንጌል ፕሪንስፕል – መሰበር፣ መፍሰስ፣ “መባከን” ነው።
ሕይወታችንን፣ ጊዜያችንን፣ ገንዘባችንን . . . ለጌታ ስንሰጥ በሰው መስፈርት እንደ መባከን ሊቆጠር ይችላል። ነገር ግን ለጌታ ክብር የተደረገ ሁሉ መባከን አይደለም ማትረፍ ነው። ምክንያቱ በሰማያት ለመታሰብያ ይጻፋልና። ጌታ ከእኛ የሚፈልገው ሕይወታችንን በእግሩ ሥር እንድናፈስስ ነው። ከአልዓዛር ሞት ሁኔታና ከማርያምና ከማርታ ሁኔታ እንደምናየው ቤተሰቡ ድሀ እንደሆነ ነው። አንዲት ሳንቲም በዚህ ቤተሰብ ዋጋ አላት። ታድያ ለምን ባከነ? ኢየሱስን “ጌታ”ብሎ ጠርቶት የማያውቅ ይሁዳስ ምን አለ? ሌሎችስ? አሥራ ሁለቱም ደቀ መዛሙርት “መባከን”፣ “ጥፋት” እንደሆነ አመኑበት። በተለይ ለይሁዳ (የዓለም ምሳሌ) እንኳንና ሽቶ ውኃም ቢሆን ኖሮ መባከን ነው። ጌታ ዓለምን (ይሁዳን) ወደደ እንጂ በዓለም አልተወደደም። በዓለም ልብ ጌታ ለጌታ ሥፍራ የለም፤ በዓለም ሲተመን ጌታን ማገልገል እንደ መባከን ይቆጠራል። ስለሆነም ዛሬ አንዳንዶች “እከሌ ጴንጤ ባይሆን ምን ዓይነት ሰው ይሆን ነበር? ትልቅ ደረጃ ይደርስ ነበር?” “እዚህ ቤተ ክርስቲያንከምትባክን ምናለ ሌላ የሚጠቅምህን ሥራ ብትፈልግ?” እያሉ የሚናገሩ አይታጡም። ጌታ ኢየሱስ “ሰው ዓለሙን ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል?” (ማቴ. 16፥26)