በኮሮና ምክንያት በየቤታችሁ የተቀመጣችሁ ቅዱሳን ሁሉ! እንኳን ለብርሃነ ትንሳኤው አደረሳችሁ!
ጎልጎታ በሮም ሥልጣን የተፈረደባቸው ወንጀለኞች በስቅላት የሚገደሉባት ስፍራ ስለነበረች ኢየሱስ ወደዚያ መወሰዱ ለኢየሩሳሌም ኗሪዎች አዲስ ነገር አልነበረም፡፡ ምናልባት አዲስ የሚሆነው አወዛጋቢ ስብዕና የነበረው መሰቀሉ ነበር፡፡ እርሱን ለማየት በጎልጎታ ዙርያ የተሰበሰቡትም ግንዛቤ የተለያየ ነበር፡፡ ለሮማ ወታደሮች በሁለት ዓመጸኞች መካከል የተሰቀለ ወንጀለኛ፤ ለፈሪሳውያን ህዝቡን ያበጣበጠ አሳች የሚገባውን ፍርድ ማግኘትና ሴራቸው መሳካት፣ ለጲላጦስ የጻድቅ ሰው ደም በከንቱ መፍሰስ (ማቴ. 27፥24)፤ ለደቀመዛሙርቱ የሚወዱት ጌታቸው ብቻ ሳይሆን የተስፋቸውም አብሮ መሰቀል የፈጠረባቸው ስሜት ተስፋ መቁረጥና ጥልቅ ሐዘን ነበር፡፡በጎልጎታ የነበሩ ሰዎች ስሜት የተዘበራረቀ ቢሆንም የኢየሱስ ስሜትስ እንዴት ነበር? መስቀል ላይ ተቸንክሮ፣ በቃላት ሊገለጽ በማይቻል ስቃይና ጣር ውስጥ ነበር፡፡ ሆኖም ስሜቱ ከስቃዩ በላይ፣ ከሁኔታዎች በላይ ተልዕኮው ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ ይህም በተናገራቸው ሰባት የመጨረሻ ቃላት ማየት ይቻላል፡፡ በዚህ ክፍል መካከል አንዱን እንመለከታለን፡- “ተፈጸመ”
“ተፈጸመ” በግሪኩ ቃል “ተሌኦ” ይለዋል፡፡ ይህም አንድን ተልዕኮ ማከናወንን፣ መጨረስን፣ መፈጸምን ወይም ማሟላትን ያመለክታል፡፡ኢየሱስ ሊሞት ጥቂት ጊዜ ሲቀረው “ተፈጸመ” ማለቱ ከስቃዬ “ተገላገልኩ” ለማለት ሳይሆን “ተከናወነልኝ” ፤ “ጨረስኩኝ” ፤ “ሙሉ ሥራ ሠርቼ መደምደሚያ ላይ ደረስኩኝ” ማለቱ ነበር፡፡
ጌታ የተሰቀለባት ዓርብ ነበረች፡፡ ከቀኑ 12 እስከ 3 PM ባለው ጊዜ ውስጥ ለሦስት ሰዓታት ያህል ጸሐይ እንደ ጨለመች፣ ጨለማም በምድር ሁሉ ላይ እንደሆነ ተጽፏል [ሉቃስ 23፥44]፡፡ ሁሉም ድንገት ሲጨልም በሰው ልብ ምን ዓይነት ፍርሃትና ሽብር እንደሚፈጠር ለመገመት አያዳግትም፡፡ ኢየሱስ ግን ምድርን ስለሸፈናት ጨለማ ሳይሆን የመጣበትን ተልዕኮ መፈጸሙን ነበር ያወጀው፡፡ ዛሬም እንዲዚሁ ምድርን ሁሉ ያዳረሰ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጨለማ በሰዎች ሁሉ ላይ ታላቅ ድንጋጤ ፈጥሯል፡፡ እኛ ግን በዚህ ውስጥ ከሁኔታዎች በላይ ሆነን ኢየሱስ በመስቀሉ ያወጀውን የምሥራች ወንጌል የማዳረስ ኃላፊነት እንዳለብን መዘንጋት የለብንም፡፡ በእርግጥ ሰዎች ሁሉ ከመቼውም ጊዜ ተስፋ የቆረጡበት ጊዜ ስለሆነ ለሰዎች ሁሉ የወንጌልን የምሥራች ማስተጋባት ጊዜው አሁን እንደሆነ በትሕትና ላሳስባችኋሁ እወዳለሁ፡፡
ምንድነው የተፈጸመው?
1. ዓለም ሳይፈጠር አስቀድሞ የታወቀው፣ ኢየሱስ ክርስቶስም ክብሩን ትቶ የመጣበት ተልዕኮ ተፈጸመ፡፡
ጌታ ኢየሱስ ደጋግሞ የተናገረለት የአባቱን ሥራ መፈጸም፣ ይህም እኛን በደሙ የመዋጀት ሥራ እንደሆነ ነው [1ጴጥ. 1፥20]፡፡ የአባቱን ፈቃድ ማድረግ፣ አባቱ የሰጠው ምግብ እንደሆነ ይናገራል፡፡ “የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው” [ዮሐ. 4፥34] ይላል፡፡ በሌላ ክፍልም “አብ ልፈጽመው የሰጠኝ ሥራ፥ ይህ የማደርገው ሥራ፥ አብ እንደ ላከኝ ስለ እኔ ይመሰክራል” (ዮሐ. 5፥36) ይላል፡፡ በአገልግሎቱ መጨረሻ በጸለየው ሊቀ ካህናዊ ጸሎትም “አባት ሆይ! እኔ ላደርገው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር አከበርሁህ” [ዮሐ. 17፥4] ብሎ ሲጸልይ እንመለከታለን፡፡ ስለሆነም ዓለም ሳይፈጠር በመለኮት የታቀደው እኛን የማዳን ሥራ በሚገባ ማከናወኑንና መፈጸሙን ያመለክታል፡፡
2. ሕጉ የሚጠይቀውን ሁሉ ኢየሱስ ማሟላቱን ያመለክታል፡፡
ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ክድንግል ማርያም ተወልዶ “ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ”፡፡ ዳዊት ከ1000 ዓመታት በፊት በመንፈስ ሆኖ ስለ ክርስቶስ የተናገረው “መሥዋዕትንና ቍርባንን አልወደድህም፤ ሥጋን አዘጋጀህልኝ፤ የሚቃጠለውንና ስለ ኃጢአት የሚቀርበውን መሥዋዕት አልሻህም፣ በዚያን ጊዜ አልሁ፦ እነሆ፥ መጣሁ፤ ስለ እኔ በመጽሐፍ ራስ ተጽፎአል፤ አምላኬ ሆይ፥ ፈቃድህን ለማድረግ ወደድሁ፥ ሕግህም በልቤ ውስጥ ነው” [መዝ. 40፥6-8] የሚለውን ትንቢታዊ ቃል ተላብሶ በመካከላችን ተገኘ [ዕብ. 10፥5-10]፡፡
በሥጋ ፍጹም ሰው ሆኖ ሕጉ የሚጠይቀውን ሊፈጽም፣ ብሎም እርሱ ራሱ ስለ እኛ የሕግ ፍጻሜ ሊሆን ስለመጣ “እኔ ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም” [ማቴ. 5፥17] ሲል እንመለከታለን፡፡ ነቢያት ሁሉ ከሩቅ ሆነው በእምነት ዓይን ያዩት፣ የተሳለሙት፣ በጉጉት የጠበቁት ታላቅ ተስፋ በእርሱ ተፈጸመ [ሉቃስ 22፥37]፡፡ እርሱ ራሱ የትንቢቶቹ ፍጻሜ ሆነ፡፡ እኛም ሕጉን የመፈጸም አቅም እንኳ ባይኖረንም በክርስቶስ ባለን እምነት ብቻ ሕጉን እንደ ፈጸምን ይቆጠርልናል “የሚያምኑ ሁሉ ይጸድቁ ዘንድ ክርስቶስ የሕግፍጻሜ ነውና” [ሮሜ 10፥4]፡፡
3. የኃጢአት ሥርየት ለአንዴና ለመጨረሻ በክርስቶስ ደም ተፈጸመ፡፡
የክርስትና እምነት ልዩ የሚያደርገው በተፈጸመ ሥራ ላይ የተመሠረተ መሆኑ ነው፡፡ የዓለም ሃይማኖቶች ሰዎች በሥራቸው እግዚአብሔርን አባብለው ለመጸደቅ ጥረት የሚያደርጉባቸው ከወንጌል እውነት ርቀው የሚደበቁባቸው ዋሻዎች ናቸው፡፡ ሃይማኖቶችም የመዳን ማረጋገጫና ዋስትና ስለማይሰጧቸው ሁሌ ራሳቸውን እንደ ኮነኑ ይኖራሉ፡፡ እኛ ግን ክርስቶስ ተፈጸመ ብሎ ባተመው የማዳን ሥራ “አሁን በክርስቶስ ላሉ ኩነኔ የለባቸውም” ተብሎልናልና ደስ ይበለን፣ እግዚአብሔር ይመስገን፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ደሙን አፍስሶ፣ የሕጉን demand ያሟላና እግዚአብሔር አብን ያረካ የደሙ መሥዋዕት ለአንዴና ለመጨረሻ በማቅረብ ዋጅቶናል፡፡ ኃጢአታችንን ወደ ራሱ አስተላለፎ፣ ተቀጥቶበታል፤ ጽድቁንም ወደ እኛ አስተላልፎ በጽድቁ ጻድቃን አድርጎናል [2ቆር. 5፥21]፡፡
ይህንን የወንጌል እውነት በዘመኑ የኮምፑዩተር ቋንቋ ብገልጸው ደስ ይለኛል፡፡ ኢየሱስ የኃጢአታችንን ዶሴ [File} በደሙ DELETE ካደረገ በኋላ ሕይወቱን፣ ጽድቁን፣ ቅድስናውን፣ ብቃቱን በሕይወታችን ላይ ጫነ፣ Download አደረገ፡፡ ስለሆነም ጴጥሮስ “ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ፤ በመገረፉ ቁስል ተፈወሳችሁ” ይለናል [1ጴጥ. 2፥24]፡፡
“ተፈጸመ” ብሎ ሲል ኢየሱስ ክርስቶስ የመጣበት ባለ ሁለት ዘርፍ ተልዕኮን አከናወነ፣ ፈጸመ ማለት ነው፣ እነዚህም፦
1. የጠፋነውን መፈለግ [ሉቃ. 19፥10፤ 1ጢሞ. 1፥15፤ ገላ. 4፥4፤ 1ዮሐ. 3፥5]
2. የዲያብሎስን ሥራ ማፍረስ [1ዮሐ. 3፥9]
ክርስቶስ እኛን የመቤዠት ሥራ በሚገባ መፈጸሙንና ለማስረገጥ እግዚአብሔር ቢያንስ አራት ምልክቶችን ሰጥቷል፡፡
1ኛ. የቤተ መቅደስ መጋረጃ ለሁለት መተርተሩ = ይህም ወደ እግዚአብሔር መቅረብ እንችል ዘንድ የጽድቅ ደጅ መከፈቱን ያመለክታል፡፡
2ኛ. የክርስቶስ ከሙታን መነሣቱ = ኃጢአት፣ ሞትና ዲያብሎስ መሸነፋቸውን ያመለክታል፡፡
3ኛ. ኢየሱስ በታላቅ ክብር ማረጉና በአባቱም ቀኝ መቀመጡ = እግዚአብሔር በክርስቶስ ሥራ መርካቱንና ደስ መሰኘቱን ያመለክታል፡፡
4ኛ. በዓለ ሃምሳ [ጴንጠቆስጤ] = የመንፈስ ቅዱስ መውረድ ወንጌል እንድታውቅጅ ለቤተ ክርስቲያን [ለእኛ] ኃላፊነት መሰጠቱን ያሳያል፡፡
“ተፈጸመ!” ሲለን ለደህንነታችን ጉዳይ መላእክትም ሆነሰዎች አንዳች የሚጨምሩት ወይም የምኪቀንሱት ነገር አለመኖሩን ያረጋግጣል፡፡
አሁን ከእኛ የሚጠበቀው ይህን እውነት አምነን በኢየሱስ ሥራ ላይ ማረፍ፡፡
በእውነት ልባችን በዚህ ሊያርፍ ይገባል፣ ዘላለማዊ ዕረፍት የሚባለውም ይህ ነው፡፡ ደግሞም በዚህ እውነት ያላረፈች ነፍስ በዚህም ሆነ በወዲያኛው ዓለም ምንም ዓይነት ዕረፍት አይኖራትም፡፡ ይህን የማዳን ሥራ መላእክቶች ወይም ሌሎች ፍጡራን ሳይሆኑ ራሱ እግዚአብሔር በኢየሱስ የፈጸመው ሥራ ስለሆነ አስተማማኝ ነው [ሮሜ 3፥25]፡፡ ታዲያ እርሱ “ተፈጸመ” ብሎ አትሞት ሳለ ሰዎች በሥራ ለመጽደቅ ደፋ ቀና ማለታቸው ለምን ይሆን?
4. “ተፈጸመ” – የኃጢአት፣ የሞትና የዲያብሎስ ሥልጣን ተሻረ፣ [ቈላ. 1፥13፤ 2፥14-15]
ድሮ በበደላችንና በኃጢአታችን ሙታን ነበርን፣ በማይታዘዙት ላይ ለሚሠራው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ እንመላለስ ነበር፣ እግዚአብሔር ግን በምሕረቱ ባለጸጋ ስለሆነ፣ ከወደደን ከታላቅ ፍቅሩ የተነሣ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን [ኤፌ. 2]፡፡ አሁን በእኛ ውስጥ ስለ በጎ ፈቃዱ መፈለግንና ማድረግን የሚሠራ እግዚአብሔር ነው፤ ክርስቶስ በፈጸመውም ሥራ ወደ አብ መቅረብ ችለናል፡፡
የስቅለት ቀን ዓርብና በማግሥቱ ቅዳሜ-ስዑር የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት ለተከታዮቹም፣ ለወዳጆቹም ትልቅ ሽንፈት መስሎ ነበር፡፡ አንዳንዶቹም ተስፋ ቆርጠው ወደ ኤማሆስ መንደር በማምራት ላይ ነበሩ፤ በጥልቅ ተስፋ መቁረጥ ላይ እንደነበሩም የፊታቸው መጠውለግ ያስታውቅ ነበር፡፡ እርሱ እየሰማ “እኛ ግን እስራኤልን እንዲቤዥ ያለው እርሱ እንደ ሆነ ተስፋ አድርገን ነበር” እያሉ ያወሩ ነበር [ሉቃስ 24፥21]፡፡ በጉዞአቸው ላይ ኢየሱስ አብሮአቸው ይጓዝ የነበረ ቢሆንም አላወቁም ነበር፡፡ ዛሬም ጌታ “እኔ ከእናንተ ጋር ነኝ፣ አትፍሩ” እያለን በተስፋ መቁረጥ ጎዳና እየተጓዝን የሽንፈት ቃል የምንናገር ስንቶች እንሆን? አሁንም የምሥራች! ዓለም በኮሮና ቫይረስ በተናወጠችበት በዚህ ሰዓትም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው! አትፍሩ! “እግዚአብሔር ሕዝቡን አይጥልምና፥ ርስቱንም አይተውምና” [መዝ. 94፥14]፡፡
ሊሞት ጥቂት ደቂቃ ሲቀረው “ተፈጸመ” ማለቱ የሞት ፍርሃት በእርሱ ኃይል እንዳልነበረው ያመለክታል፡፡ ኢየሱስ ሞቶ ሲቀበር ሞትና የሞት ፍርሃት ከእርሱ ጋር ተከፍነው መቃብር ወርዷል፤ እርሱ በሦስተኛው ቀን ሲነሣ ግን እነሱ በዚያው ተቀብረው ቀርተዋል፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን መነሣት ሰዎች ስለሞት የነበራቸውን ጥያቄና መልስ አስገኝቶአል፡፡ ዊልያም ሼክስፒሪ የተባለው እንግሊዛዊ ባለቅኔና ጸሐፌ-ተውኔት እንዲህ ሲል ይናገራል “Fear of death is worst than death itself.” ኮሮና ቫይረስ በዓለም ላይ ከፈጠራቸው ሥጋቶች ውስጥ የሞት ፍርሃት ዋናው ነው፡፡ ኢየሱስ ግን የሞትን ፍርሃት ሽሮአል! “ተፈጸመ” [ዕብ. 2፥14]፡፡
ሉቃስ 23፥44 ላይ “ስድስት ሰዓትም ያህል ነበረ፥ ጨለማም እስከ ዘጠኝ ሰዓት በምድር ሁሉ ላይ ሆነ፥ ጸሐይም ጨለመ” ይላል፡፡ ኢየሱስ ግን በዚያ ጨለማ እስጥ “ተፈጸመ!” የሚል ቃል አውጆቻል ብለናል፡፡ ዓለም እየተናወጠች ባለችበት በአሁኑ ሰዓት ለእኛም የተሰጠ የድል ቃል ይኸው ነው! ስለሆነም “ተፈጸመ” እና “ኢየሱስተነስቷል” – የመስቀሉና የትንሣኤውን ድል ለጨለማው ዓለም ማበሠር የእኛ ኃላፊነት ነው!
በመጨረሻም የመስቀሉን “ተፈጸመ” አምኖ የትንሣኤውን ድል ተካፋይ የሆነ አማኝ ወደፊት የሚሰማው ሌላ “ተፈጸመ” አለ፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ የምንሰማው “ተፈጸመ” ግን ከመስቀሉ ሳይሆን ከዙፋኑ ነው! ጌታ በክብር ይመጣል [ራዕ. 21፥6]፡፡ “መንፈሱና ሙሽራይቱም፦ ና ይላሉ። የሚሰማም፦ ና ይበል! አሜን፥ ጌታ ኢየሱስ ሆይ ና!”
ወንድሞቼና እህቶቼ! የኮሮና ቫይረስ በመጣበት ይመለሳል! እኛም በቅርቡ ተሰብስበን አብረን ጌታን እናመልካለን! እስከዚያ
በያለንበት ተግተን እንጸልይ! በእምነትም እንበርታ!