ወደ እግዚአብሔር የተዘረጉ እጆች።

በሰሞኑ ህማማት ሳምንት በዛሬው የሐሙስ ቀን ጌታ ኢየሱስ ከአሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ጋር እራት ሊበላ በማእድ የተቀመጠበት እንደነበረ መጽሐፍ ይነግረናል።

አርብ ቀን ደግሞ ከደቀ መዝሙሮቹ አንዱ ይሆነኛል ብሎ በመረጠው ይሁዳ ተከድቶ አልፎ ተሰጠና አሰቃይተውት በመስቀል ላይ ሰቅለው ገደሉት።ኢሳይያስ እንደሚል እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ: እርሱ ስለ መተላለፋችን ቆሰለ ስለ በደላችንም ደቅቆ ሞተ ተቀበረም (ኢሳ. 53:5,6) ። በሶስተኛውም ቀን ሞትን ድል አድርጎ ተነሳ: በድል አድራግነትም ወደ ሰማይ በማረግ በአባቱ ቀኝ ተቀመጠ (የሐ.ሥራ 2:33)። 1ቆሮ. 8:6 ” ለእኛስ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ እኛም ለእርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ አለን: ነገር ሁሉም በእርሱ በኩል የሆነ እኛም በእርሱ በኩል የሆንን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶሰ አለን” ተብሎ እንደ ተጻፈ አምነን የዳን ሁላችን በሰማይ ካሉት አማልክት ሁሉ ልዩና ድንቅ የሆነ አምላካችን በአንድ ውድ ልጁ በኩል በሆነልን እምነት ከማይጠፋ ዘር ተወልደን ልጅነትን ከሙሉ ስልጣን ጋር ተቀበልን።
በአሁን ወቅት የእነማን እጆች ወደ ጌታ እግዚአብሔር ተዘረጉ ለሚለው ትንሽ አሳብ ማስቀመጥ ወደድኩ።

“መኳንንት ከግብጽ ይመጣሉ; ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች”።

መዝ 68:31
  1. ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ዘረጋች። በአገራችን ታሪክ በመንግሥት እዉቅና ተሰጥቶ ሶስቱም ታላላቅ የጏይማኖት ተቋማት (ኦርቶዶክስ; የወንጌል አማኛችና ሙስልሞች) አንድ ላይ ተስማምተው ለጸሎት ለልመናና ለምልጃ ወደ እግዚአብሔር የቀረቡበት ወቅት ከዚህ በፊት እንደነበረ አላስታውሰም። በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት 110 ሚሊየን የኢትዮጵያን ሕዝብ ወክለው ከምሽቱ 3-4 ወይም 9-10 ሕዝቡም በየቤቱ በቤተሰብ ሆነው እየተባበሩ ለአንድ ወር የሚቆይ ብሔራዊ ጸሎት ትናንት በኢትዮጵያ እንደ ተጀመረ ሳትሰሙ አልቀራችሁም። ከላይ የተጠቀሰውን የእግዚአብሔርን ቃል “ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች” የሚለዉን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ያረጋገጠም ነው።
  2. አለም ሁሉ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ዘርግታለች። ይህ ታላቅ ጏያል የሁሉ ፈጣሪ የሆነ አምላካችን ከፍጥረታቱ ሁሉ attention ያገኘበት ወቅት ቢኖር አሁን ነው። እግዚአብሔር እራሱ በእጁ በፈጠራት አለም ትንሽ ግምት እንኳ እስከማይሰጠው ድረስ በነገር ሁሉ ወደ ጎን ከመገፋቱም በላይ በብዙዎች አይን የተናቀበት ወቅትም ነበር። የግብጽ ንጉሥ ፈርኦን እስራኤልን እለቅ ዘንድ እግዚአብሔር ማን ነው ብሎ እንደ ነበር አለምም የአምላካችንን ሂልውና ለመካድ የድፍረት ሙከራ አድርጋለች። በተመሳሳይ ኢትዮጵያን ያስተዳደሩ የደርግ ባለስልጣናትም ይህንኑ ስህተት በማድረግ እግዚአብሔር የለም እስከ ማለት የደርሱበት ወቀት ቢኖርም እርሱ በዘላለማዊ ዘፋኑ ተቀማጭ በመሆኑ ስልጣናቸውን ለሌሎች ሰጥቶ አስወገዳቸው። አሁን ያለች አለማችን ዛሬ የአምላካችንን ዘላለማዊ ሂልውና ሳትወድ ተቀብላው እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር በመዘርጋት ላይ ትገኛለች።
  3. ገዢዎች ነገሥታት ባለስልጣናትና መኳንንት ሁሉ እጆቻቸውን ወደ እግዚአብሔር ዘርግተዋል። ለኮቪድ 19 መፍትኼ ለመሰጠት ያልተሞከረ ነገር የለም። ብዙ መሯራጥ ሆኗል; ሆኖም ተስፋ የሚጣልበትና የተገኘ መፍትኼ ጨርሶ የለም። የጣሊያን አገር መሪ ሰሞኑን እንዳሉት ለኮቪድ 19 መፍትሔ የሚሆን መድጏኒትም ለማግኘት ባለመቻላችን የመጨረሻ መፍትኼ ያለው ከእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ እናምናለን ብለዋል።
  4. ቤተክርሰትያንም እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ዘርግታለች።
    4.1 በንሰሃ ወደ እግዚአብሔር ፊት ለመቅረብ 2ዜና 7:14
    4.2 አይኖቻችንን ለልመና ወደ እግዚአብሔር ለማንሳት በ2ዜና 20:12 “ይህን የመጣብንን ወገን እንቃወም ዘንድ አንችለቀም; የምናደርገውንም አናውቅም: ሆኖም አይኖቻችን ወደ አንተ ናቸው።
    4.3 እግዚአብሔርን ለማመስገን መዝ 50:23
    4.4 መንገዳችንን ለእግዚአብሔር አደራ ለመሰጠትና በእርሱም ለመታመን መዝ 37:5-6
    4.5 ሳናቋርጥ ለመጸለይ ሉቃ 18:1-7
    4.6 ሁል ጊዜ ደስ ለመሰኘት ፊል 4:4
    4.7 ፈቃዱን ለመረዳት 1ተሰሎንቄ 5:16
    በዚህ ሁሉ እጆች ከነገድ ከቅዋንቋ ለጸሎት ለልመናና ለምልጃ ወደ እግዚአብሔር በብዛት የተዘረጉበት ወቅት ቢኖር አሁን ይመስለኛል። ወደ እኔ ጩኽ እኔም እመልስልሃለሁ አንተም የማታውቀውን ታላቅና ጏይለኛን ነገር አሳይሃለሁ ብሎ በተገባልን ተሰፋ መሠረት ወደ እርሱ ለልመና የተዘረጉ እጆች ታላቅ የሆነና ፈጣን መልስ እንዲያስገኙልን በእምነት ሆነን እንጠብቅ አሜን ይሁንልን። ቅዱሳን ሁላችሁ ተባረኩልኝ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *