እግዚአብሔርን በመተማመን መጠበቅ | በፓስተር ዶ/ር አለማየሁ

“እግዚአብሔርን በመተማመን የሚጠባበቁ ግን ጏይላቸውን ያድሳሉ” ኢሳ 40:31

እግዚአብሔር አምላካቸው የሆነላቸው ሕዝቦች ክፉ ዘመናትን የተሻገሩት እርሱን ተማምነው በትዕግሥት በመጠበቅ እንደነበረ ታሪክ ይነግረናል። በተለይ የእስራኤል ልጆች አራት መቶ ሰላሳ አመታት በግብጽ አገር ቆይተው የመጨረሻዎቹን የስቃይና የመከራ አመታቶቻቸውን በትዕግሥት ማለፍ የቻሉት እግዚአብሔር አንድ ቀን ከዚህ አስከፊ መከራ በጸናች ክንዱ ሊታደገን ይችላል ብለው በመተማመን ጠብቀውት እንደነበረ ግልጽ ነው።
ኢሳይያስ ምዕራፍ 40 ሁለተኛው የመጽሐፉ ክፍል የሚጀምርበት እንደሆነ ይታወቃል። ሐዋርያው ዮሐንስ በራዕይ 4:22 ላይ ወደ ፊት ስለሚሆነው ነገር እንደ ጻፈ ሁሉ ነቢዩ ኢሳይያስም በስድስተኛው ምዕተ ዓመት (ዓ ቅ ክ) ተማርከው ስለሚወሰዱትና ወደ ፊት ስለሚሆነው ነገር በማመልከት የጻፈው ነው።

በአንድ ወቅት እስራኤል ወይም ያዕቆብ ተስፋ ከመቁረጡ የተነሳ “መንገዴ ከእግዚአብሔር ተሰውራች ፍርደም ከአምላኬ አልፋለች” (ኢሳይያስ 40:27) በማለት ድምጹን ያሰማበት ወቅት ነበር። ሆኖም ነቢዩ ኢሳይያስ ለምን እንድህ ትላለህ ትናገራለህ ? አላወቅህምን ? አልሰማህምን ? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ የምድርም ዳርቻ ፈጣሪ ነው ብሎ ይናገረዋል(40:28)።

በዚህ በኢሳይያስ ምዕራፍ 40 የምንተማመንበት እግዚአብሔር ማነው ?

  1. መንገድ ተስተካክሎ ተሠርቶለት በሰረገላ እንደሚሄድ የከበረ የነገሥታት ንጉሥ (40:3-4) ነው
  2. ሕያው ቃሉ ለዘላለም ጸንታ የሚትኖር (40:8)
  3. ውኆችን በእፍኙ የሰፈረ ሰማይንም በስንዝሩ የለካ: (40:12)
  4. የምድርንም አፈር በመስፈርያ ሰብስቦ የያዘ: ተራሮችን በሚዛን ኮሮብቶችንም በሚዛኖች የመዘነ (40:12)
  5. መንፈሱ በማንም የማይታዘዝ: አማካሪና አስተማሪም የለሌው(40:13)
  6. የፍርድን መንገድና እውቀትን ማንም የማያስተምረው (40:14)
  7. የማስተዋልን መንገድ ማንም የማያሳየው
  8. አሕዛብን በገንቦ እንዳለች ጠብታ የሚያይ: በሚዛን እንዳለ ትንሽ ትቢያ የሚቆጥር (40:15)
  9. አሕዛብ ሁሉ በፊቱ እንዳልነበሩ የሚያደርግ: ከምናምን እንደሚያንሱ እንደ ከንቱ ነገር የሚቆጥራቸው (40:17)
  10. በማንም የማይመሰል: ወይም ከማንም ማስተያየት የማይቻል (40:18)
  11. በምድር ክበብ ላይ የሚቀመጥ; በኦርሷም የሚኖሩ እንደአንበጣ የማቆጥራቸው
  12. ሰማያትን እንደ መጋረጃ የሚዘረጋቸው እንደ ድንኳንም ለመኖሪያ የሚዘረጋቸው (40:22)
  13. አለቆችንም እንዳልነበሩ የምድርንም ፈራጆች እንደ ከንቱ ነገር የሚያደርጋቸው (40:23)
  14. በሰማይ ያሉትን የፈጠረ: ሠራዊታቸውን በቁጥር የሚያወጣ; ሁሉንም በየስማቸው የሚጠራቸው(40:26)
  15. በጏይሉ ብዛትና በችሎቱ ብርታት አንድስ እንኳ የማይታጣው (40:26)

በኢትዮጵያ በነበርንበት ወቅት በ1979 ዓ ም ድንገት በደረሰብኝ አደጋ ተጎድቼ ከሥራ ወጣሁ። በእምነቴ ምክንያት የአብዮቱ ደጋፊ አይደለም ተብዬ በ32 አመት ጡረታ አስወጡኝ። በባለቤቴ የአስተማሪ ደሞዝና በጡረታ ገቢ $250 የኢት ብር ሶስት ልጆች እያሳደግን የማጣት ኑሮ ቀጠልን። በዚህ ሁኔታ ለሶት አመት ስንኖር እግዚአብሔር ፈጥኖ ይደርስልናል በሚል እርሱን በመታመን በትዕግሥት ጠበቅነው። እግዚአብሔርም በታማኝነቱ በጊዜው በድንቅ ሁኔታ ከተፍ አለልንና ወደ ከበረው ሙያዬና ሥራዬም ተመልሽ ከአገር እስከወጣሁ ድረስ በመልካም ኖርን። ተማምነንበት ስንጠብቀው ለልጆቹ ፈጥኖ ደራሽ እንደሆነ እኔ ምስክር ነኝ። ዛሬም ባለሁበት ሁኔታ ማን ሊደርስልኝ ይችላል ለምትሉ ወጌኖቼ እርሱ የታመነ ስለሆነ ፈጥኖ ይደርስላችጏል።

ይህን ግሩምና ድንቅና አምላክ በመተማመን
ስንጠባበቀው;

  1. ጏይላችን ይታደሳል
    የአለማችን ኑሮ የምናልፍባቸው የኑሮ ተግዳሮቶች መንፈሳዊ ውጊያ ተጨምሮበት እጅግ የሚያደክም ቢሆንም እግዚአብሔርን ተማምነን ሰንጠባበቅ በመንፈስ ቅዱሱ ጏይላችን ይታደሳል። ጏይላችን ከመታደሱ የተነሳ ከፊታችን ያለውን ማንኛውንም መከራና ፈተና በአሸናፊነት እንድናልፍ ጸጋ ይለቀቅልናል: ይህን የኮሮናን ዘመን ለመሻገር ልዩ ጏይሉ እንደሚለቀቅልን ተስፋ አደርጋለሁ።
  2. እንደ ንስር በክንፍ እንወጣለን
    የንስር ተፈጥሮአዊ ሁኔታው ከሚበሩ ወፎች ሁሉ ለየት ይላል። ከመሬት ተነስቶ ከፍታን ለመውረስ በጣም ይቀነዋል። እግዚአብሔርን ተማምነን ስነጠብቅ በቀላሉ ከፍታን ለመውረስ ጸጋው ይለቀቅልናል።
  3. ይሮጣሉ አይታክቱም
    ሁላችንም እንደምንረዳው በተለይ የሰሜን አሜርካ ኑሮ በሩጫ የተሞላ እንደሆነ ግልጽ ነዉ። ሆኖም እግዚአብሔርን በመታመን የተጠባበቁትና ኑሮአቸውን የመሩትን ሁሉ እርሱ አላሳፈራቸውም።
  4. ይሄዳሉ አይደክሙም
    በተለይ ሠራተኞች ሆነው ቅዱሳን ለእግዚአብሔር መንግሥት የወንጌልን አደራ ለመወጣት ሲተጉ በረጅም ሰለሚጓዙ አይደክሙም።

ወጌኖቼ በማንኛው ችግርና ፈተና የሚናልፍ ሁላችን እግዚብሔርን በመተማመን ስንጠብቀው በማንኛውም ሁኔታ ዉስጥ ፈጥኖ ይደርስልናል። እኔ ምስክር ነኝ ለእኔና ለቤተሰቤ ደርሶልን አይቻለሁና; ዛሬም አልተለወጠም በዚህ በሚያሰጋ በሚያስፈራና በሚያስጨንቅ በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት በሙሉ ልባችን ታምነንበት በትዕግሥት እንጠብቀው እርሱም በድንቅ ሥራው ያስደንቀናል። እወዳችጏለሁ ተባረኩ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *