ስፍራህን አትልቀቅ | በዶ/ር ድልነሳው ቸኮል

የእሴይ ልጅ ዳዊት፥ ገና ለግልላጋ ወጣት በነበረበት ጊዜ፥ በቤተሰብ ውስጥ ስፍራና ቦታ ያልተሰጠው ከመሆኑ የተነሣ በዚያ ማኅበረሰብ ውስጥ እጅግ ዝቅተኛ ግምት የሚሰጠውን የእረኝነት ሥራ እንዲሠራ በቤተሰቡ ተመድቦ፥ ውሎው እና አዳሩ በዱር በገደሉ የአባቱን በጎች መጠበቅ ነበር። ዳዊት በአደራ የተሰጡትን በጎች፥ በሙሉ ልቡ፥ የሚያስፈልጋቸውን በማድረግ ይንከባከባቸው ነበር፡፡ ከዚያም አልፎ፥ ለበጎቹ ደኅንነት የራሱን ሕይወት እንኳ ለአደጋ አሳልፎ ለመስጠት ሁል ጊዜ ዝግጁ ነበር። ይህ በቤተሰቡ ትልቅ ዋጋ ያልተሰጠው ዳዊት፥ የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣት፥ ለነፍሱ ሳይሳሳ፥ ከአንበሳና ከድብ ጋር አንገት ላንገት እየተናነቀ በጎቹን ከአደጋ ይጠብቃቸው ነበር። ከዚህም የተነሣ፥ ከተሰጠው አደራ አንዳች እንኳ አላጎደለም።

ዳዊት በተሰጠው የእረኝነት ሥራው እየተጋ ሳለ፥ እግዚአብሔር ለእስራኤል የመጀመሪያ ንጉሥ እንዲሆን የጠራው ንጉሥ ሳዖል፥ ከእግዚአብሔር መንገድ ይልቅ የራሱን መንገድና ክብር ፈላጊ ስለሆነ፥ እግዚአብሔር የልቡን ፈቃድና አሳብ የሚፈጽምለትን ሌላ ሰው ንጉሥ አድርጎ እንዲቀባለት ነብዩ ሳሙኤልን አዘዘው። ነብዩ ሳሙኤልም በእግዚአብሔር ምሪት ወደ እሴይ ቤተስብ በመሄድ በውጫዊ አቋማቸውና ገጽታቸው የሰውን ቀልብ የሚስቡትን ለንጉሥነት ሊቀባ ተነሣ፡፡ እግዚአብሔር ግን አስቁሞት በወላጆቹና በወንድሞቹ ፊት ዋጋ ያልተሰጠውን፥ ነገር ግን በእርሱ የተመረጠውን እረኛውን ዳዊትን ንጉሥ አድርጎ እንዲቀባው አዘዘው። እግዚአብሔርም ዳዊት በወጣበትና በገባበት ቦታ ሁሉ ድልን ያጎናጽፈው ጀመር። እግዚአብሔር የዳዊትን መንገድ ማቅናቱና ማከናወኑ፥ በሳዖል ልብ ውስጥ፥ በዳዊት ላይ፥ ከፍተኛ የሆነ ቅናትና ጥላቻ አሳደረ፤ ዳዊትንም ለሞት ይፈልገው ጀመር። ከነቤተሰቡ በሄደበት ቦታ ሁሉ እስክ ሞት አሳደደው። ዳዊት ግን፥ እስከ ሳዖል ኅልፈት ድረስ፥ ተስፋ አስቆራጭ ለነበረው ፈተናና ስቃይ እጁን ሳይሰጥ፥ በእግዚአብሔር ጸጋ በጽናት አለፈ።

ከንግሥናው በኋላ፥ እግዚአብሔር ለዳዊት ሦስት ታላልቅ ድሎችን አጎናጽፎታል። ሳዖል ከሞተ በኋላም፥ በየቦታው ተበታትነውና ተበጣጥሰው የነበሩ አሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች በአንድነት ተሰባስበው በፈቃዳቸው ወደ ዳዊት መጡ፤ እግዚአብሔር ቀድሞ እንደተናገረው፥ ዳዊት ንጉሣቸው ሆኖ በአንድነት እንዲመራቸው ከእግዚአብሔር ጋር በመስማማት ከዳዊት ጋር ውል ገቡ (2ኛ ሳሙ 1:1-5:23)። ይህ የመጀመሪያው ድል፤ ሁሉም ነገዶች እንደ አንድ ሕዝብ ጠንክረው በብርታት እንዲቆሙ አድርጓቸዋል። ሁለተኛው ድል ደግሞ ዳዊት ለእስራኤል ሕልውና ዋስትና የሆነውን መንፈሳዊ መነቃቃት ማምጣቱ ነው፡፡ ይህንንም ያደረገው ከዋናው ከተማ ውጭ በግለስብ ቤት ውስጥ የተቀመጠውን የአምላኩን ታቦት እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት በሌዋውያን አሸክሞ ወደ ኢየሩሳሌም በማምጣት ነው፡፡ ይህም በሕዝቡ ዘንድ ትልቅ መንፈሳዊ መነቃቃትንና መታደሰን አመጣ ( 2ኛ ሳሙ 6:1-7:29):: ንጉሥ ዳዊት የእግዚአብሔርን ታቦት፥ የእስራኤል ዋና ከተማ ወደ ሆነችው ወደ ኢየሩሳሌም አስመጥቶ ሕዝቡም ለእግዚአብሔር ለአምላካቸው የሚገባውን መሥዋዕትና አምልኮ እንዲያቀርቡ አደረገ፡፡ ይህም በሕዝቡ ዘንድ ታላቅ ደስታንና ዋስትናን ፈጠረ። አስደናቂ ተሓድሶ!!!

በንጉሥ ሳዖል ዘመን፥ እስራኤላውያንን ዙሪያቸውን ከበው በጭካኔ ሲመዘብሯቸውና ሲያስጨንቋቸው የነበሩትን መንግሥታት፥ በእግዚአብሔር ትእዛዝ መሠረት ወጥቶ አደጋ በመጣል፥ ፍልስጥኤምን፥ ሞዓብን፥ ሶርያን፣ ዔዶምን፥ አማሌቅን፥ አሞንንና ሌሎችንም ወገኖች በታላቅ ኃይል መታቸው፡፡ እግዚአብሔርም በሄደበት ስፍራ ሁሉ ድልን እንዲቀዳጅ አደረገው። ይህም እግዚአብሔር ለዳዊት የሰጠው ሦስተኛው ድል ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ዳዊት በመላው እስራኤል ንጉሥ ሆኖ፥ ሕዝቡ ዘወትር ትክክለኛ ፍትሕ እንዲያገኝ የሚችለውን ሁሉ ያደርግ ነበር (2ኛ ሳሙ 8:1-10:9)። ከ2ኛ ሳᎀኤል ምዕራፍ 1 እስከ ምዕራፍ 10 እንደምናነበው፥ ዳዊት አስደናቂ የሆኑ ሊሎች ተግባራትንም ፈጽሟል፡፡ የተበታተኑትን አሰባስቦ አንድ ሕዝብ ሆነው እንዲቆሙ በማድረግ፥ እንዲሁም የእግዚአብሔር ክብርና ፈቃድ መገለጫ የሆነውን የቃል ኪዳን ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም አስመጥቶ መንፈሳዊ ተሓድሶና መነቃቃት እንዲከሰት በማድረግ፥ ከዚያም በላይ እስራኤልን ከበው ያስጨንቋቸው የነበሩትን ከአምስት በላይ የሆኑ ነገሥታትን ድል በመንሣት፥ እስራኤል ለመጀመሪያ ጊዜ በትልቅ እረፍት እንዲኖሩ አድርጓል።

እግዚአብሔር ዳዊትን በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ለሕዝብ እረኛ፥ ለሠራዊቱ ደግሞ የጦር መሪ ሆኖ ከፊት እየቀደመ የእግዚአብሔርን ጦርነትን እንዲዋጋ ስለጠራው፥ ንጉሥ ዳዊት በተሰለፈበት ጦርነት ሁሉ ከድል ወደ ድል በሚያስደንቅ ፍጥነት ይሻገር ነበር። በጥንት ዘመን ነገሥታት ሁሉ በበረዶና በዝናብ ወራት ለጦርነት ስለማይወጡ ንጉሥ ዳዊትም ከነጦሩ በበረዶና በዝናብ ወራት ያርፍ ነበር። የበረዶውንና የዝናቡን ወቅት በእረፍት ካሳለፉ በኋላ ግን በጸደይ ወራት ከነጦራቸው ይወጡ ነበር። በአንድ ወቅት ግን፥ ንጉሥ ዳዊት፥ መላውን የእስራኤልን የጦር ሠራዊትና አለቆቻቸውን በማሰለፍ እርሱ እንደ ጦር መሪ ከፊት ቀድሞ በመራራት የእግዚአብሔርን ጦርነት ሊዋጋ ሲገባው፥ በኢየሩሳሌም በቤተመንግሥት መቆየትን መረጠ (2ኛ ሳሙ 11:1)።

ንጉሥ ዳዊት የእግዚአብሔርን ጦርነት መዋጋትን ትቶ በኢየሩሳሌም ቤተ መንግሥት በነበረበት ወቅት፥ ከእለታቱ በአንዲቱ “እንዲህም ሆነ፤ ወደ ማታ ጊዜ ዳዊት ከምንጣፉ ተነሣ፥ በንጉሥም ቤት በሰገነት ላይ ተመላለሰ፤ በሰገነቱ ሳለ አንዲት ሴት ስትታጠብ አየ፤ ሴቲቱም መልከ መልካም ነበረች። ዳዊትም ልኮ ስለ ሴቲቱ ጠየቀ፤ አንድ ሰውም። ይህች የኤልያብ ልጅ የኬጢያዊው የኦርዮ ሚስት ቤርሳቤህ አይደለችምን? አለ። ዳዊትም መልእክተኞች ልኮ አስመጣት፤ ወደ እርሱም ገባች፥ ከርኵሰትዋም ነጽታ ነበርና ከእርስዋ ጋር ተኛ፤ ወደ ቤትዋም ተመለሰች። ሴቲቱም አረገዘች፥ ወደ ዳዊትም “አርግዤአለሁ!” ብላ ላከችበት”(2ኛ ሳሙ 11:2-5)። ንጉሥ ዳዊት ቤርሳቤህ እንዳረገዘች ባወቀ ጊዜ ይህ ችግር በመንግሥቱ ሊያመጣ የሚችለውን ቀውስ ተረዳ፡፡ አባትዋ ኤልያብ እና ባለቤቷ ኦርዮ ከሰላሳ የዳዊት ኃይለኛ ጀግና ጄኔራሎች መካከል ሲሆኑ፥ የአባቷ አባት አኪጦፌል ደግሞ፥ ቃሉ ምድር ጠብ የማትል የዳዊት አማካሪ ነበር (2ኛ ሳሙ 23:34):: ንጉሥ ዳዊት ኃጢአቱ በሰው ፊት ሳይገለጥ እንዲቀር ለማድረግ፥ ባሏን ከጦር ሜዳ አስጠርቶትና በብዙ መጠጥ እንዲሰክር አድርጎ ከእርሷ ጋር እንዲተኛ በዙ ጣረ፡፡ ለእግዚአብሔርና ለሕዝቡ ታማኝ የሆነው ኦርዮ ግን ለዳዊት “ታቦቱና እስራኤል ይሁዳም በጎጆ ተቀምጠዋል፤ ጌታዬ ኢዮአብና የጌታዬም ባሪያዎች በሰፊ ሜዳ ሰፍረዋል፤ እኔ ልበላና ልጠጣ ወይስ ከሚስቴ ጋር ልተኛ ወደ ቤቴ እሄዳለሁን? በሕይወትህና በሕያው ነፍስህ እምላለሁ! ይህን ነገር አላደርገውም” የሚል መልስ ሰጠው (2ኛ ሳሙ 11:11)። ዳዊት ግን ይህ ዘዴ እንዳልሠራለት ሲያውቅ፥ ኃጢአቱን ለመሸፈን በንጹሑና በታማኙ በኦርዮ ላይ ሞት ፈርዶ ተላልፎ ለጠላት እንዲሰጥ ትእዛዝ የሚሰጥ ደብዳቤ በራሱ እጅ አስይዞ ወደ አለቆቹ ላከው። በትዛዙም መሠረት ኦርዮ ለሞት ተላልፎ ተሰጠ።

ኧረ ለመሆኑ እንደ ልቤ የተባለለት ዳዊት ለዚህ ውድቀት እንዲጋለጥ ያደረገው ምክንያት ምን ይሆን? የዳዊት የመጀመሪያ ስሕተት ኃላፊነቱን ችላ ማለቱ አልነበረምን? ከእግዚአብሔር የተሰጠውን የጦር ሠራዊቱን የመምራት ኃላፊነቱንና ስፍራውን ለቆ፥ ጦሩን ያለ ዋና መሪ ከጠላት ጋር እንዲጋጠሙ በሜዳ ትቷቸው እርሱ ግን በቤተ መንግሥት ማረፍን መረጠ። ከተጠራበት የሕይወት ጥሪ ማለትም የእግዚአብሔርን ጦርነት ከመዋጋት ይልቅ ለራሱ እረፍትን በመምረጡ፥ ራሱን ከእግዚአብሔር ጥበቃ ክልል ማውጣቱን እንረዳለን፡፡ ይህም ሕይወቱንና ቤተሰቡን ቁልቁል ከጣለው የኃጢአት ወጥመድ ውስጥ እንዲወድቅ ምክንያት ሆነው። ገና ብላቴና ሳለ፥ ለእግዚአብሔር እና ለሕዝቡ አስደናቂ ቅናትና ፍቅር የነበረው ከመሆኑ የተነሣ፥ ሰዎችን ሁሉ ያሽብር የነበረውን ጎልያድን እንኳ ለመግጠም፥ ምንም እንኳ ወንድሞቹ ከጦር ሜዳው እንዲሄድ ቢወተውቱትና ቢያስገድዱት፥ እርሱ ግን ነቅነቅ ሳይል እራሱን አሳልፎ የሰጠ ሰው ነበር። ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር ለሕዝቡ እረፍትን ሰጥቶ ነበር። ታዲያ ለጌታና ለሕዝቡ የነበሩት ፍቅርና ቅናት ወዴት ገብተው ነው ከእግዚአብሔር የተሰጠውን ሕዝቡን ከጠላት ጦር የመጠበቅና የመምራት ኃላፊነቱን ወደ ጎን ተውት አድርጎ ለራሱ በቤተ መንግሥት ማረፍን የመረጠው? ጌታ በዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ ምዕራፍ 2 የቀድሞ ፍቅሯን ስለመጣልዋ እንደወቀሳት፥ የብዙ ሥራዎችና ድሎች ባለቤት እንደሆነችው እንደ ኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን እርሱም የቀደመውን ለእግዚአብሔር እና ለሕዝቡ ያለውን ፍቅሩንና ቅናቱን ጥሎ ይሆንን?

ጌታ እኛን ከሞት ወደ ሕይወት አምጥቶ በአባቱ ቀኝ ከስቀመጠን በኋላ፥ በዚህ በተጠራንበት ስፍራችን ጸንተን መቆም የምንችለው አጽንተን ዕለት በዕለት በእምነት እርሱን ስንፈልገው አንዲሁም ጽድቁንና መንግሥቱን በቃሉ፥ በጸሎትና በቅዱሳን ኅብረት አጥብቀን በመፈለግ የእምነት ገድላችንን ስንዋጋ ነው። ዛሬስ የእያንዳዳችንን ጊዜ የሚያልፈው እግዚአብሔር በልጁ ባስቀመጠን ስፍራችን ሆነን እርሱ የሰጠንን ኃላፊነት በመወጣት ነው ወይስ የሰጠንን የሕይወት ዘመን ጥሪያችን የሆነውን እርሱን በነገር ሁሉ መፈለግ ትተን ለራስችን ምቾትና ደስታ እያዋልነው ይሆን? ስፍራን መልቀቅ ጠንካራውን፣ ቆራጡንና ጀግናውን ዳዊትን አዳልጦ ቁልቁል እንደወረውረው እኛም ስፍራችንን በለቀቅንበት ጉዳይ ላይ ፈጥነን ንስሐ ገብተን ከወደቅንበት እንደገና ተነሥተን በፊቱና በስፍራችን እንድንቆም ሊያደርግ የሚያስችለን ጸጋ በልግስና ወደ ሚሰጠው አምላካችን እንቅረብ።

ጸሎት

ጌታ ኢየሱስ ሆይ እባክህ ከምቾታችን፣ ከስንፍናችን፣ ከግደየለሽነት ወጥተን አንተ ባስቀመጥከን ስፍራ ሆነን በቃልህ ድምፅህን እየሰማን፣ ፊትህን በጸሎት በመፈለግና ከቅዱሳን ቤተሰቦቻችን ጋር ቅዱስ ኅብረትን እንድናደርግ የእያንዳንዳችንን መንፈስ ታነቃቃ ዘንድ የሚደግፈውንና የሚያቀናውን ጸጋህንም አትረፍርፈህ ለእያንዳንዳችን እንድትሰጠን በስምህ እንለምንሃለን። አሜን!!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *