በውኑ እኔን የሚያቅተኝ ነገር አለን? | በፓስተር ኤፍሬም ላእከማርያም

“እነሆ፥ እኔ የሥጋ ለባሽ ሁሉ አምላክ እግዚአብሔር ነኝ፤ በውኑ እኔን የሚያቅተኝ ነገር አለን?”

ኤር. 32፥27

እስራኤል እግዚአብሔርን አልሰማ ሲሉ፣ ከእግዚአብሔርም መንገድ ሲወጡ ወደ ባቢሎን እንደ ተወሰዱ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፡፡ በዚህ ምዕራፍ ቁ. 23 ላይ “ነገር ግን ቃልህን አልሰሙም በሕግህም አልሄዱም፥ ያደርጉም ዘንድ ካዘዝሃቸው ሁሉ ምንም አላደረጉም፤ ስለዚህ ይህን ክፉ ነገር ሁሉ አመጣህባቸው” ይላል፡፡ ቀጥሎም ራሱ እግዚአብሔር ሲናገር (ቁ. 33) “ፊታቸውንም ሳይሆን ጀርባቸውን ወደ እኔ መለሱ፤ እኔም በማለዳ ተነሥቼ ሳሰተምራቸው ተግሣጽን ይቀበሉ ዘንድ አልሰሙም” ስለዚህ “እነሆ፥ ይህችን ከተማ ለከለዳውያን እጅና ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ” አለ (ቁ.28)፡፡እግዚአብሔርን ካለ መስማት የተነሣ ሁሉንም በምርኮ ወደ ባቢሎን እንደሚያስግዛቸው፣ ከለዳውያንም ከተማቸውን እንደሚገዟት አስቀድሞ ተናግሯል፡፡ በአንድ በኩል እግዚአብሔር በምድሪቱ ላይ ካስተላለፈው ፍርድ የተነሣ ከንጉሡ ከሴዴቅያስ ጀምሮ ሁላችሁ በምርኮ ወደ ባቢሎን ትጋዛላችሁ፣ ከተማይቱም በከለዳውያን ሥር ትወድቃለች ይላቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ነቢዩ ኤርምያስን በአናቶት ያለውን እርሻ ከአጎቱ ልጅ ከአናምኤል እንዲገዛ፣ የውል ወረቅቱንም በሸክላ ዕቃ ውስጥ እንዲያስቀምጥ ሲያዝዘው እንመለከታለን፡፡ በዚህም ምክንያት ኤርምያስ ግራ የተጋባ ይመስላል፡፡ ነገር ግን ተናጋሪው እግዚአብሔር ስለሆነ ኤርምያስ እንዲህ ይለዋል [ቁጥር 17 -21]፡- “አቤቱ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ እነሆ፥ አንተ ሰማይንና ምድርን በታላቅ ኃይልህና በተዘረጋች ክንድህ ፈጥረሃል፥ ከአንተም የሚያቅት ነገር የለም፤ ለብዙ ሺህ ምሕረት ታደርጋለህ . . . . ስምህ ታላቅና ኃያል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው። በምክር ታላቅ በሥራም ብርቱ ነህ፤ ለሁሉም እንደ መንገዱና እንደ ሥራው ፍሬ ትሰጥ ዘንድ ዓይኖችህ በአዳም ልጆች መንገድ ሁሉ ተገልጠዋል። . . “ነቢዩ ኤርምያስ በቁ. 17 ላይ የእግዚአብሔርን ታላቅነት በተመለከተ የተናገረውን ለማስረገጥ ይመስላል፡- “እነሆ፥ እኔ የሥጋ ለባሽ ሁሉ አምላክ እግዚአብሔር ነኝ፤ በውኑ እኔን የሚያቅተኝ ነገር አለን?” የሚለው፡፡ዛሬ ግራ ለተጋባህበት ጉዳይ እግዚአብሔር “በውኑ እኔን የኢያቅተኝ ነገር አለን?” ብሎ ቢጠይቅህ መልስህ ምን ይሆናል? “ሙሴን፦ በውኑ የእግዚአብሔር እጅ አጭር ሆነ? አሁን ቃሌ ይፈጸም ወይስ አይፈጸም እንደ ሆነ አንተ ታያለህ አለው” ብሎታል [ዘኁ. 11፥23]፡፡ በእምነት ጉዞ መጀመሪያውና መጨረሻውን እንጂ መሃል ላይ ያለውን የፈተና ጊዜ ስለማይታየን ግራ እንጋባለን፡፡ እግዚአብሔር በሰጠን ተስፋ ቃል ቆመን የሚሆንልንን እንጂ በዚህና በዚያ መሃል ያለውን የተግሣጽ፣ የትምሕርት፣ የፈተና፣ የመጥራትና የማደግ ጊዜ አይነግረንም፡፡ እስራኤልን ከግብጽ ሲያወጣቸው ማርና ወተት የምታፈሠውን እንደሚያወርሳቸው ነበር የተናገራቸው፡፡ ጉዞ ከጀመሩ በኋላ ግን መሃል ላይ ምድረበዳ የሚባል ለካ ይጠብቃቸው ኖሯል? ብዙ መንጠባጠብ ሆነ፡፡ ንጉስ ዳዊት እግዚአብሔርን “መሓሪና ይቅር ባይ፣ ጻድቅም ነው” ይለዋል (መዝ. 112፥4)፡፡ ሐዋርያው ያዕቆብም “ጌታ እጅግ የሚምር የሚራራም ነውና” ይለዋል (ያዕ. 5፥11)፡፡ እናም ወደ ባቢሎን ካስማረካቸው በኋላ እንደገና በምሕረት ሲያስባቸው እንመለከታለን፡፡ [ቁ. 37 – 41] ያለውን አብረን እናንብብ፦

“እነሆ፥ በቍጣዬና በመዓቴ በታላቅም መቅሠፍቴ እነርሱን ካሳደድሁባት አገር ሁሉ እሰበስባቸዋለሁ፥ ወደዚህም ስፍራ እመልሳቸዋለሁ፥ ተዘልለውም እንዲኖሩ አደርጋለሁ፤እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ።ለእነርሱም ከእነርሱም በኋላ ለልጆቻቸው መልካም ይሆንላቸው ዘንድ ለዘላለም እንዲፈሩኝ አንድ ልብና አንድ መንገድ እሰጣቸዋለሁ።ለእነርሱም ከማደርገው በጎነት አልመለስም ስል፥ ከእነርሱ ጋር የዘላለምን ቃል ኪዳን እገባለሁ፤ ከእኔም ዘንድ ፈቀቅ እንዳይሉ መፈራቴን በልባቸው ውስጥ አኖራለሁ።ለእነርሱም መልካምን በማድረግ ደስ ይለኛል በእውነትም በፍጹም ልቤና በፍጹም ነፍሴ በዚህች ምድር እተክላቸዋለሁ”

እግዚአብሔር ማሻገርን ብቻ ሳይሆን መምራትም፣ ማድረስም ይችላል፤ ማስወጣትን ብቻ ሳይሆን መመለስንም ይችላል፡፡ ዛሬ እያንዳንዳችን የምናልፍባቸው የማያመቹ ሁኔታዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ሆኖም በእምነት እግዚአብሔርን ብንጠብቅ ይበጀናል፡፡ የፈተና፣ የተግሳጽ፣ የመጥራትና በእምነት የማደግ ጊዜ እንዳለ ሁሉ የመታሰብ፣ የመጎብኘት፣ የመሻገር ጌዜም አለ፡፡ እንደ ጨለመብን አንቀርም፣ አንድ ቀን ብርሃን ይወጣል፡፡ ሰውን ከምድር አፈር የሚያበጅ፣ በአፍንጫውም የሕይወትን እስትንፋስ እፍ ብሎ ሕያው ነፍስ ያለውን ሰው መፍጠር የሚችል እንደ አምላካችን ያለ ማን አለ? ዮኒቨርስን ክሌለ ነገር መፍጠር የሚችል፤ ፍጥረትን ሁሉ ካለ መኖር ወደ መኖር ማምጣት የሚችል እንደ አምላካችን ያለ ማን አለ? ታድያ ያንተ / ያንቺ ጉዳይ ምን ያህል ትልቅ ነው? አምላካችንስ የሚያቅተው ነገር አለ? እስኪ በጸሎት በምሥጋና ሆነህ በእርሱ ፊት ቁጭ በል! ጉዳይህንም በፊቱ አቅርብ! እርሱ የሥጋ ለባሽ ሁሉ አምላክ እግዚአብሔር ነው፤ በውኑ የሚያቅተው ነገር አለን?

ጌታ ቀንህን / ቀንሽን ይባርክ!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *