ኅብረታችን | በፓስተር ዶ/ር ኤፍሬም ላእከማርያም

ክርስትና በክርስቶስ አምኖ የዘላለምን ሕይወት ማግኘት ነው፡፡ ክርስትና በክርስቶስ ከእግዚአብሔርና ከሌሎች ሰዎች ጋር ኅብረት ማድረግ ነው፡፡ በዚህ ምድር አያሌ ማኅበራት ያሉ ቢሆንም የክርስትና ኅብረት ግን ለየት የሚያደርገው እግዚአብሔር ራሱ የሚገኝበት ኅብረት መሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም ዮሐንስ በጻፈው 1ኛ መልዕክቱ ላይ፦

“እናንተ ደግሞ ከእኛ ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ ያየነውንና የሰማነውን ለእናንተ ደግሞ እናወራላችኋለን። ኅብረታችንም ከአባት ጋር ከልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው!” ብሏል

፩ኛ ዮሐ ፩፡፫

እዚህ ላይ “ኅብረት” የሚለውን ቃል አዲስ ኪዳን በተጻፈበት የግሪክኛ ቋንቋ “ኮይኖኒያ” ይለዋል፡፡ ይህም እኛ አማኞች በከርስቶስ ሆነን ከእግዚአብሔርና ከእርስ በርሳችን ጋር ያለንን መንፈሳዊ ኅብረት ያመለክታል፡፡ ይህም ኅብረት የወይን ግንድ ከቅርንጫፍ ጋር፣ ቅርንጫፎችም ከጠቅላላው አካል ጋር ባለው ግኑኝነት ምሳሌ ተገልጾአል [1ቆሮ. 12፥12፤ ቈላ. 1፥18፤ ዮሐ. 15፥1-5]፡፡

ክርስቶሳዊ ኅብረት አካላዊ፣ ማኅበራዊ፣ መንፈሳዊ ነው፡፡ ክርስቶሳዊ ኅብረት ሰማያዊም ምድራዊም ነው፡፡ ክርስቶሳዊ ኅብረት ሁለት አቅጣጫዎችን ያመለክታል:- ወደ ላይ ከእግዚአብሔር ጋር፤ ወደ ጐንም ከቅዱሳን ጋር። አንዱን ከሌላው መነጠል ፈጽሞ አይቻልም፡፡ ከአንዱ ጋር ያለን ግኑኝነት ከተበላሸ ሌላውም ይበላሻል ማለት ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግኑኝነት ከተዛባ፣ ከሰውም ጋር ያለን ይዛባል። ከሰው ጋር ያለን ኅብረት ከተበላሸ ከእግዚአብሔርም ጋር ያለን ኅብረት ይበላሸዋል [ማቴ. 5፥23_24]፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ሰላም ነኝ እያልን ከሌሎች ጋር ጸበኛ ነኝ ማለት አንችልም፡፡

ይሁን እንጂ በወደቀ ዓለም ስለምንኖርና ገና ያልተዋጀ/የወደቀ ሥጋ የለበስን በመሆኑ ልንደርስበት የሚገባንን አቅጣጫ ለማሳየትና የእግዚአብሔርንም መስፈርት [Standard] ለማመልከት እንጂ በምድር እስካለን ድረስ ፍጹማን እንሆናለን ማለቴ አይደለም፡፡  

ክርስቶሳዊ ኅብረት ጥበቃንና ጥንቃቄን የሚጠይቅ ነው። በተለይ ከወገኖች ጋር የሚኖረን ኅብረት በአንድ አፍታ የሚያድግ ሳይሆን ራስን በቃሉ መነጽር እያዩ አዳማዊ ባሕርዮችን በመገረዝ; ራስንም በማሸነፍ፣ መልካም የሆነውንና ጌታ የሚከብርበትን በፈቃደኝነት እየመረጡ በመንፈስ ቅዱስ እገዛ የሚያዳብሩት ጉዳይ ነው፡፡ 

በ17ኛው ክፍለ ዘመን የነበረ ጆን ዶን የተባለ ሰባኪ/ጸሐፊ ይህን ብሏል፡፡

“ማንም ሰው በራሱ ደሴት አይደለም፣ አንዱ ብቻውን ሙሉ አይደለም፣ አንዱ ለሌላው በጣም ያስፈልገዋል”

ጆን ዶን

እኛም እንደዚሁ የሙሉው አካል ማለትም የክርስቶስና የቤተ ክርስቲያን ክፍሎች ነን እንጂ በራሳችን ሙሉ አይደለንም። አንዳችን ለአንዳችን እናስፈልጋለን፡፡

“ዳሩ ግን አሁን ብልቶች ብዙዎች ናቸው አካል ግን አንድ ነው: ዓይን እጅን፦ አታስፈልገኝም ልትለው አትችልም፥ ወይም ራስ ደግሞ እግሮችን፦ አታስፈልጉኝም ሊላቸው አይችልም”

1ቆሮ. 12:20-21


በአዲስ ኪዳን “እርስ በርሳችሁ” / ‘እርስ በርሳችን” የሚሉ ሁለት ሐረጎች ከ70 ጊዜ በላይ መጠቀሳቸውን ልብ እንበል፡፡

ራሳችን በራሳችን ሙሉ ልንሆን ስለማንችል እግዚአብሔር በመጀመሪያ ከራሱ ጋር፣ ቀጥሎም ከሌሎች ቅዱሳን ጋር ሕብረት ሰጠን፡፡ በዚህም ሕብረት ውስጥ በረከቱንና ሕይወትን እንዳዘዘ ዳዊት ይናገራል [መዝ. 133]፡፡

አሁን በገጠመን ሁኔታ ቴክኖሎጂውን ተጠቅመን አገልግሎት መስጠትና መቀበል ብንችልም በአንድ ሥፍራ ተከማችተን ማምለካችንን ፈጽሞ ሊተካ አይችልም፡፡ ስለሆነም ትልቅ ነገር እንደጎደለብን አንርሳ። የተሰጠን ኅብረት እንደ ቀላል ነገር ቆጥረነው ከነበረ ተሳስተናል። ምን ያህል ውድ እንደሆነ እንድናስተውል ዕድል ያገኘን ይመስለኛል፡፡ ስለሆነም እግዚአብሔር ቀኖቹን እንዲያሳጥርልንና ቶሎም እንዲያገናኘን  አጥብቀን እንጸልይ፡፡ ሰሞኑም መንፈስ ቅዱስ ወደ ልባችን የሚያመጣቸውን ወንድሞችንና እህቶችን እያሰብን ስለ እነርሱ ጌታን እናመስግን።

ጌታ ይባርካችሁ!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *