የጥሞና ቃል ክፍል 3

የይበቃኛል መንፈስ/ Spirit of Contentment

1ጢሞ. 6፥6-12

“ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው

ወደ ዓለም ምንም እንኳ አላመጣንምና፥

አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፥ እርሱ ይበቃናል፤

ዳሩ ግን ባለ ጠጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ።

ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፥ አንዳንዶች ይህን ሲመኙ፥ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ።

አንተ ግን፥ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ከዚህ ሽሽ፤ ጽድቅንና እግዚአብሔርን መምሰል እምነትንም ፍቅርንም መጽናትንም የዋህነትንም ተከታተል።

መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል፥ የተጠራህለትንም በብዙም ምስክሮች ፊት በመልካም መታመን የታመንህለትን የዘላለምን ሕይወት ያዝ”

ፊል. 4፥11

“የምኖርበት ኑሮ ይበቃኛል ማለትን ተምሬአለሁና፣ መዋረድንም አውቃለሁ መብዛትንም አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና መራብንም መብዛትንና መጉደልን ተምሬአለሁ፤ ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ”

ሕይወት በዚህ ዓለም ማዕቀብ በሌለው የጥድፊያ ጉዞ ላይ ትገኛለች። በዚህም የጥድፊያ ጉዞ ኃብትና ጥሪት፣ ዝናና ታዋቂነት፣ ሥልጣንና ኃይል ሰዎች የሚሮጡባቸው፣ የሚጠሟቸውና የሚጋደሉባቸው የእሽቅድድም እውነታዎች ናቸው። ይህንን ሕልም ግቡ ለማድረስ በሚያደርጉት ጥድፊያም ብዙዎች ለጭንቀትና ለመከራ ተዳርገዋል። ነገር ግን የኑሮአችን ማዕከል ምድራዊና ቁሳዊ ነገር ሳይሆን እግዚአብሔር እንዲሆን ከላይ የተጠቀሱት ክፍሎች ያሳስቡናል። ቅዱስ ጳውሎስ አዕምሮ ያለው ሰው ፈጽሞ ሊክደው የማይችል አውነት አስቀምጦልናል፦ “ወደ ዓለም ምንም አላመጣንምና፣ አንዳችም ልንወስድ አይቻለንም”። ድሆችም ሆኑ ባለ ኃብቶች በሞት ሲከወኑ ከሬሳ ሳጥን በቀር ምንም ይዘው መሄድ አይችሉም። ይህ የሕይወት እውነታ ነው። ስለዚህ እውነት ጳውሎስ ብቻ ሳይሆን ጌታም እንዲህ ብሎ ይናገራል። “ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል?” (ማቴ. 16፥26)።   “ስለ ነፍሳችሁ በምትበሉትና በምትጠጡት፥ ወይም ስለ ሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ፤ ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ አይበልጥምን? . . . እንግዲህ። ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል” (ማቴ 6፥25-33)።

በዚህ ዓመት ለሕይወትዎ የሚያስፈልገው ዋና ነገር ምን እንደሆነ ተረድተው አካሄድዎን ያስተካክሉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *