የጥሞና ቃል ክፍል 2

“ወደ እግዚአብሔር ቤት በገባህ ጊዜ እግርህን ጠብቅ ለመስማት መቅረብ ከሰነፎች መሥዋዕት ይበልጣልና . . . እግዚአብሔር በሰማይ፥ አንተም በምድር ነህና በአፍህ አትፍጠንበእግዚአብሔርም ፊት ቃልን ይናገር ዘንድ ልብህ አይቸኵል ስለዚህም ቃልህ ጥቂት ትሁን”

(መክ. 5፥1-2)

 

ይህንን ቃል አንብቤ በዘመናችን ካለው የጸሎትም ሆነ የአምልኮ ልምምድ ጋር ሳነጻጽረው እውነት ለመናገር በጣም ያስፈራኛል። ልብንና ኩላሊትን በሚመረምር፣ ሁሉን በሚችል፣ ሁሉን በሚያውቅና ዳርቻና ወሰን ሳይኖረው ሁሉ በሁሉ በሆነ አምላክ ፊት ሥጋ ለባሽ ሰው ምን ብሎ መናገር ይችላል? ይህን ስል በፍጹም መናገር አያስፈልግም እያልኩ አይደለም፤ ለምን? “ወደ እኔ ጩህ” (ኤር. 33,3) ያለው እርሱ ነውና። ነገር ግን ቅዱስ ዳዊት “የአፌ ቃልና የልቤ አሳብ በፊትህ ያማረ ይሁን” (መዝ. 19፥14) እንዳለ በእግዚአብሔር ፊት ስንሆን የምንናገረው ቃል ጥራትና የምንናገርበትን መንፈስ መመርመር አስፈላጊ መሆኑን ለማመልከት ብቻ ነው። ዳዊት በሌላ ክፍል “ቃሌ ለእርሱ ይጣፍጠው . . .” (መዝ. 104፥34) ይላል።

በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 17፥1-8 ባለው ክፍል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ይዞ ወደ ተራራ እንደወጣ፣ በፊታቸውም ፊቱ እንደ  ጸሐይ በርቶ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆኖ እንደ ተለወጠ፣ ሙሴና ኤልያስም ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ እንደታዩአቸው ተጠቅሶአል። በዚህ ጊዜ “ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን ጌታ ሆይ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ብትወድስ፥ በዚህ ሦስት ዳስ አንዱን ለአንተ አንዱንም ለሙሴ አንዱንም ለኤልያስ እንሥራ አለ” ይላል። በመሠረቱ ክፍሉ ሙሴና ኤልያስ ከኢየሱስ ጋር መነጋገራቸን እንጂ ምን ምን እንደተባባሉ አልተጻፈም። እነ ሙሴ የተነጋገሩት ከጌታ እንጂ ከጴጥሮስ ጋር አልነበረም። አዲስ ኪዳን የተጻፈበት የግሪኩ ትርጉም ግን ጴጥሮስ “መልሶ. . . መለሰ . . . መልስ ሰጠ” ብሎ ይላል። ከጌታ ጋር ሲነጋገሩ የነበሩት ሙሴና ኤልያስ ሲሆኑ ጴጥሮስ ጣልቃ ገብቶ ያልተጠየቀውን ሲመልስ ይታያል። ጴጥሮስ የሰነፎች መሥዋዕት አቅርቦ ይሆን? እኛስ አጥርተን ሳንሰማ አሊያም ጌታ ሳይጠይቀን ምላሽ እየሰጠን ይሆን? በቅዱስ አምላክስ ፊት አፋችን ያመጣልንን ዘባዝበን ይሆን?

ጌታ ቢፈቅድና ብንኖር በዚህ ዓመት ለአፋችን/ምላሳችን ጥንቃቄ ለማድረግ በቅዱስ አምላክ ፊት የቆጡን የባጡን ላለመናገር የአዲስ ዓመት ውሳኔ እናድርግ። ልባችንና አፋችን አንድ እንዲሆኑ እንጂ ዳዊት “በአፋቸው ይባርካሉ በልባቸውም ይረግማሉ” (መዝ. 62፥4) ያለው እንዳይሆንብን፤ ያዕቆብም “ከአንድ አፍ በረከትና መርገም ይወጣሉ። ወንድሞቼ ሆይ፥ ይህ እንዲህ ሊሆን አይገባም” (3፥10) ያለውን አስተውለን በዚህ ዓመት አፋችን/ምላሳችን ለእግዚአብሔር የተቀደሰ እንዲሆን እንወስን!

“ምላሴ ጽድቅህን ሁልጊዜም ምስጋናህን ይናገራል” (መዝ. 35፥28)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *