የጥሞና ቃል ክፍል 6

ሌሊቱ ይነጋል!

“ሙሴም በባሕሩ ላይ እጁን ዘረጋ፣ እግዚአብሔርም ሌሊቱን ሁሉ ጽኑ የምስራቅ ነፋስ አምጥቶ ባሕሩን አስወገደው:: ባሕሩንም አደረቀው፣ ውኃውም ተከፈለ፤ የእሥራኤልም ልጆች በባሕሩ መካከል በየብስ ገቡ፣ ውኃውም በቀኛቸውና በግራቸው እንደ ግድግዳ ሆነላቸው…ንጋትም በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር በእሳትና በደመና ዓምድ የግብጻውያንን ሠራዊት ተመለከተ…አወከ…አሠረ…ወደ ጭንቅም አስገባቸው፣ ግብጻውያንም እግዚአብሔር በግብጻውያን ላይ ይዋጋላቸዋልና ከእሥራኤል ፊት እንሽሽ አሉ” (ዘጸ. 14፣21-25)

በዚህ ቃል ውስጥ እጅግ የሚያጽናና ሀሳብ አለ። የእግዚአብሔር አሠራር መንገዱ እጅግ ብዙ ቢሆንም ከአሰራሩ አንዱን ያሳየናል።

ይህም ሥራው በሌሊት ማለትም በጨለማ እንደነበር እናያለን። ሌሊት እንቅስቃሴ ሁሉ የሚያቆምበት፣ ብዙ ነገር የሚዘጋበት ጊዜ ነው። ለእስራኤል በሌሊት የሚታያቸው የጠላት ሰልፍ ብቻ ነበር። ለጊዜው የማይታይ ግን ድንቅ ስራ ጊዜ ነበር። አዎን ለእሥራኤል ጨለማ የነበረ ቢሆንም ለእግዚአብሔር ግን የሥራ ሰዓት ነበርና። “ሌሊቱን ሁሉ” በሌሊት፣ ሁሉ ነገር የተኛ በሚመስልበት ሰዓት፣ የኛ ነገር ያበቃ፣ ያከተመ በሚመስልበት ሰዓት ለካ ለእግዚአብሔር የሥራ ጊዜ ነው። ተስፋ ያደረግነው ነገር የሞተ በሚመስልበት ጊዜ፣ ምንም የሚታይ ነገር የሌለ በሚመስልበት ሰዓት እግዚአብሔር ግን በሥራ ላይ ነው። “በጊዜው ሁሉን ነገር ውብ አድርጎ ይሠራዋል፣ ያበጃጀዋልም። የእግዚአብሔር ሥራ የሚገለጸው ለሰው ሲጀምር ቢመስልም ለእግዚአብሔር ግን ሲጨርስ ይሆናል። አንተም/አንቺም በዚሁ ሁኔታ የምታልፉበት ጊዜ ይኖራል፣ አሁንም ሊሆን ይችላል። ነገር ግን የሚወዳችሁ አምላካችሁ፣ የእሥራኤል ቅዱስ አሁንም ከእናንተ ጋር ነው። ነገር ሁሉ የጨለመ ሊመስል ይችላል፣ ነገር ግን በጊዜው ብርሃን ይወጣል፣ ባሕሩም ይከፈላል፣ አንተም/አንቺም ትሻገራላችሁ፣ ለእግዚአብሔርም የሙሴን ቅኔ ትቀኛላችሁ (ዘጸ. 15)። “ንጋትም በሆነ ጊዜ” ሌሊት ብቻ ሆኖ አልቀረም፣ “ንጋትም ሆነ” በነጋ ጊዜ እሥራኤል ራሳቸውን ያገኙት ተሻግረው ነበር።ሌሊቱ ይነጋል፣ ጨለማው ይወገዳል። ከላይ ያለውን ቃል አንብበው ይጸልዩ!

ጌታ ይባርክዎ!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *