በመንፈስ ተመላለሱ!
(πνεύματι περιπατειτε) ገላ. 5፡16
በጥንታዊው የግሪክ ቋንቋ (Coine Greek) “ፔሪፓቴኦ” የሚለው ቃል በአዲስ ኪዳን ውስጥ 95 ጊዜ ተጽፎ እናገኘዋለን። ትርጉሙም መሄድ፣ መመላለስ፣ መኖር፣ ራስን መግራት ማለት ሲሆን ቅዱስ ጳውሎስ በገላትያ 5፣16 ላይ “πνεύματι περιπατειτε ኒዩማቲ ፔሪፓተይተ” “በመንፈስ ተመላለሱ፣ በመንፈስ ኑሩ፣ በመንፈስ ሂዱ፣ በመንፈስ ራሳችሁን ምሩ” በሚል ቃል ለአማኞች ትልቅና መሠረታዊ ትምሕርት ያስተላልፋል፤ በኤፌሶን 5፡18 ላይም “መንፈስ ይሙላባችሁ…” ብሎ ይናገራል።
ጌታን ከማወቃችን በፊት በበደላችንና በኃጢአታችን ምክንያት መንፈሳችን ሙት ነበር (ኤፌሶን 2፣1)። ጌታን ካገኘን በኋላ ግን የእግዚአብሔር መንፈስ ወደ ውስጣችን ገብቶ አዲስ ሕይወትን ሰጠን፣ በመንፈስም ሕያዋን ሆንን (ሮሜ 8፣10-11)፤ ያን ጊዜ መንፈሳዊ ዓይናችን ተከፈተ፣ ያኔም ማን መሆናችን ብቻ ሳይሆን የማን መሆናችንን ተረዳን። ሰው ጌታን ባያውቅ ራሱን አያውቅም፣ ስለዚህም በ16ኛው ክፍለ-ዘመን ከነበሩት የተሐድሶ መሪዎች አንዱ ጆን ካልቪን (John Calvin) “ሰው በመጀመሪያ እግዚአብሔርን ካላወቀ ራሱን (ማንነቱን) በእርግጠኝነት ወደ ማወቅ ደረጃ ፈጽሞ አይደርስም” ብሏል። ታድያ በዘመናችን እግዚአብሔርን የማያውቁ ሰዎችና የEvolution ሊቃውንት ነን ባዮች በእግዚአብሔር መልክ የተፈጠረውንና ክቡር የሆነውን ሰው “እንስሳ ነው” ወይም “ከእንስሳት አንዱ ነው” ብለው ቢናገሩ ምን ያስደንቃል?
እርግጥ ነው የሰው ልጅ በራሱ ጥረት እግዚአብሔርን ሊያውቅ አይችልም፣ እግዚአብሔርን ካላወቀ ደግሞ የራሱን ማንነትና ለምን ዓላማ እንደተፈጠረም ማወቅ ፈጽሞ አይችልም። ምክንያቱም ከውድቀት በኋላ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል የኃጢአት ግድግዳ ስላለ (ኢሳ. 59፣1-8)፤ በዚህም ምክንያት ሰው ከእግዚአብሔር በመራቁ መንፈሳዊ ነገሩና አምላኩን የማወቅ ችሎታው ሁሉ የጨለመ ስለሆነ ነው። ጌታ ኢየሱስን እንደግል አዳኛችንና ጌታችን አድርገን ስንቀበል ግን በመንፈስ ተወልደን የእግዚአብሔር ልጆች እንሆናለን (ዮሐ. 1፣11-12፤ ሮሜ 8፣14-16)፣ ስማችንም በሕይወት መጽሐፍ ይጻፋል (ራዕ. 3፣5፤ 13፣8፤ ዕብ. 12፣23)፣ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን ይኖራል፣ የነበረንንም ዓለማዊ ባሕርይ በየቀኑ እየቀረፈ የጌታን ባሕርይ ያለብሰናል፣ እየተለወጥንም እንሄዳለን። ይህም ማለት የእግዚአብሔር ልጆች የመሆን ሥልጣን (መብት) ወዲያው ጌታን ስንቀበል (በዳግም ልደት) የምናገኘው እውነት ሲሆን የሕይወት ለውጥ ግን ቀስ በቀስ የሚያድግ እንጂ ቅጽበታዊ (Instantaneous) አይደለም፣ ይህም ከቃሉ ጋር ካለን ግኑኝነትና ከመታዘዝ ጋር ተዛማጅነት አለውና።
ስለሆነም አማኝ ጌታን ካገኘበት ሰዓት ጀምሮ መንፈስ ቅዱስ በሕይወቱ ይኖራል፤ መንፈስ ቅዱስ ዳግም ለተወለደው አዲሱ ሰውም ዕድገት ይሰጠዋል፣ ያጠነክረዋል፣ ያበረታዋልም። ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ “በመንፈሱ በውስጥ ሰውነታችሁ በኃይል እንድትጠነክሩ ክርስቶስም በልባችሁ በእምነት እንዲኖር እንደ ክብሩ ባለ ጠግነት መጠን ይስጣችሁ” (ኤፌ. 3፣14-16) ይላል።ስለሆነም ጌታን ካገኘን በኋላ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወት እንዲኖረንና በመንፈስ እንድንመላለስ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው።