የጥሞና ቃል ክፍል 17

አቤንኤዘር ” . . .እስከ አሁን ድረስ እግዚአብሔር ረድቶናል . . .” 1 ሳሙ. 7፥12

        עַד־הֵ֖נָּה (ዓድ-ሔና) የሚለው የዕብራይስጡ ቃል “እስከዚህ ድረስ” ወይም “እስከ ዛሬ/አሁን ድረስ” የሚል መንታ ትርጉም ይሰጣል። አንዱ ቦታን ሲያመለክት ሁለተኛው ደግሞ ጊዜን የሚጠቁም ነው። ታሪኩም እንዲህ ነበር፦ እስራኤል በፍልስጥኤማውያን ላይ ድልን ከተቀዳጁ በኋላ ሳሙኤል አንድ ድንጋይ ወስዶ በምጽጳና በሼን መካከል እንዳኖረውና ስሙንም “አቤንኤዘር” ብሎ እንደጠራው ተጽፎአል። ይህ ከመሆኑ ከሃያ ዓመታት በፊት በእስራኤል ኢካቦድ ሆኖ ነበር ማለትም ክብር ከእስራኤል ለቅቆ ነበር፤ የእግዚአብሔርም ታቦት ተማርካ ነበርና ስለዚህም እስራኤል በጠላቶቻቸው የተመቱ ሆኑ። ከሃያ ዓመት በኋላ ግን በሳሙኤል መሪነት እስራኤል ወደ ምጽጳ ተሰብስበው በጾምና በጸሎት ሆነው ንስሐ ገቡ፣ ሳሙኤልም የሚጠባ የበግ ጠቦት ወስዶ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ፣ እግዚአብሔርም እስራኤል ወደ እርሱ እንደ ተመለሱ አይቶ ረዳቸው። ስለዚህ ፍልስጠኤማውያንን አሳልፎ ሰጣቸው። ከሃያ ዓመት በኋላ የድል ዝማሬ በእስራኤል ካምፕ ተሰማ። ይህንን የእግዚአብሔር እርዳታና ቸርነት የሚቀጥል ትውልድ እንዳይረሳ ትልቅ ድንጋይ ተክሎ “አቤነኤዜር” የሚል ጽሑፍ እንደ ጻፈበት እንመለክታለን። ይህም የእግዚአብሔር ታማኘነት የሚታይበት መዘክር ሆኖ ለትውልድ ይኖራል።

        ጅቡቲ በስደት ካምፕ በብዙ መከራ ያለፈ አንድ ወዳጄ (ዛሬ አገልጋይ ነው) ከጅቡቲ ይዞት የመጣ በትንሽ የፕላስቲክ ከረጢት ቋጥሮ ያስቀመጠውን አሸዋ አሳየኝ። ለምን ብዬ ስጠይቀው ከዚያ መከራና ቃጠሎ ያወጣኝ እግዚአብሔር ነውና ውለታውን እንዳልረሳ ምልክት ይሆንልኛል አለኝ፤ ያንን የነበርኩበትን ሕይወትና የእግዚአብሔር ታዳጊነት ያስታውሰኛል አለኝ።

እግዚአብሔር ለሁላችንም ባለውለታችን ነው። ብናስተውለውም ባናስተውለውም “እስከዚህ ድረስ እግዚአብሔር ረድቶናል”

ለሃያ፣ ሠላሳ፣ አርባ ወይም ሃምሳ ዓመታት ያህል በመከራና በችግር፤ በከፍታና በዝቅታ፣ በሚመችም በማይመችም አልፈን ይሆናል። በዚህ ሁሉ “እስከአሁን ድረስ እግዚአብሔር ረድቶናል” ክብር ለስሙ ይሁን። አቤንኤዘር የሚለው ቃል ወደኋላ ብቻ ሳይሆን ወደፊትም የሚያመለክት ቃል ነው፤ ማለትም እስከ አሁን ድረስ ታማኝ ሆኖ የረዳን ጌታ ከዚህ በኋላም ቢሆን እንደሚረዳን፣ እንደማይጥለን፣ ትናንት ያሻገረን ጌታ ዛሬም ነገም እንደሚያሻግረን ተስፋችንንና እምነታችንን የሚያድስ ቃል ነው።  ስለሆነም ይህን መዝሙር አብረን እንዘምር!

         አቤንኤዘር የእግዚአብሔር እርዳታ

          አቤንኤዘር ፈጥኖ ደርሶልናል

ከፊታችን ላለው ምንም ነገር

ትላንት ያደረገው ለዛሬ እምነት ሆኖልናል . . .

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *