የጥሞና ቃል ክፍል 21

“የእግዚአብሔር መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፥ የተሰበርውንና የተዋረደውን ልብ እግዚአብሔር አይንቅም” መዝ. 51፥17

እግዚአብሔር ለክብሩ የሚጠቀምባቸው ሰዎች የተሰበሩ ሰዎች ናቸው፤ ምክንያቱ እግዚአብሔር የሚቀበለው መሥዋዕት ከተሰበረ መንፈስና ከተዋረደ ልብ ነውና። ያዕቆብ በጵንኤል ሸለቆ ሥጋዊ ብርታቱ ከተሰበረ በኋላ፣ የጭኑን ሹልዳ እግዚብሔር ነክቶት እያነከሰ መሄድ ከጀመረ በኋላ ነበር የበረከት ሰው የሆነው፤ የእግዚአብሔርም ሐሳብ በሕይወቱ የተከናወነው። ሙሴ ዓለቱን ከመታ በኋላ ነበር ውኃው ከዓለቱ የፈለቀው (ዘጸ. 17፥6)። ሦስት መቶ የጌዴዎን ሰዎች ማሰሮዎቻቸውን ሲሰባብሩ የችቦው ብርሃን መታየት ቦግ መታየት ጀመረ፣ በጠላት ድንኳንም ፍርሃትና መንቀጥቀጥን ፈጠረ። (መሳ. 7፥19)። ጌታ ኢየሱስ አምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ባርኮ ከቆረሳቸው (ሰበራቸው) በኋላ ነበር ተባዝተው ሁሉንም አጥግበው የተረፈው ቍርሽራሽ አሥራ ሁለት መሶብ ሊሰበሰብ የተቻለው። ማርያም “እጅግ የከበረ ጥሩ ናርዶስ ሽቱ የሞላበት የአልባስጥሮስ ቢልቃጥ ይዛ መጣች፤ ቢልቃጡንም ሰብራ በራሱ (ኢየሱስ) ላይ አፈሰሰችው” (ማር. 14፥3፣ ማቴ 26፥7)። ይህ ሁሉ የመሰበርና ለእግዚአብሔር የመመቸት ውጤት ነው። በእርስዎስ ሕይወት ያልተሰበረ ነገር፣ እግዚአብሔር ያልከበረበት ነገር፤ ለእግዚአብሔር ያልተመቸ ክፍል አለ ወይ?

“እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሰማይ ዙፋኔ ነው፥ ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት የምትሠሩልኝ ቤት ምን ዓይነት ነው? የማርፍበትስ ስፍራ ምንድር ነው? እነዚህን ሁሉ እጄ ሠርታለችና እነዚህ ሁሉ የእኔ ናቸው ይላል እግዚአብሔር

ነገር ግን ወደዚህ ወደ ትሑት፥ መንፈሱም ወደ ተሰበረ፥ በቃሌም ወደሚንቀጠቀጥ ሰው እመለከታለሁ” ኢሳ. 66፥1-2

….

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *