የጥሞና ቃል ክፍል 22

“እግዚአብሔር ታላቅ እንደ ሆነ፥ ጌታችንም ከአማልክት ሁሉ እንዲበልጥ አውቄአለሁና፤

በሰማይና በምድር በባሕርና በጥልቆች ሁሉ፥ እግዚአብሔር የወደደውን ሁሉ አደረገ” (መዝ. 135፥5)

እዚህ ላይ “አውቄአለሁ” የሚለውን የቃሉ ማሰርያ አንቀጽ ልብ እንበል። ይህ የአእምሮ እውቀት ሳይሆን በሕይወት ልምምድ የሚገኝ እውቀትን ያመለክታል። ይህም ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን የግል ትውውቅ (እውቀት) የሚመለክት ነው። ከተወለድን ጀምሮ ከቤተሰብና ከአካባቢ፣ ኋላም ከትምሕርት ቤትም ከከጓደኞችም ብዙ ዓይነት እውቀትን እንገበያለን።በሃይማኖት፥ በትምሕርት፣ በባሕል፣ ከናት ከአባት እየተነገረን ስናድግ ከውስጣችን እንዲሁ ተቀርጾ የሚቀር እውቀት አለ። ነገር ግን ይህ ሁሉ የአእምሮ ዕውቀት እንጂ በግል ደረጃ እኔ አውቀዋለሁ የምንልበትና ከውስጥ ነፍሳችንን የሚያረካ ጉዳይ አይሆንም። ምናልባት “ስለ እግዚአብሔር” እናውቅ ይሆናል እንጂ እግዚአብሔርን ራሱን በግል የምናውቅበት መንገድ አይሆንም። በትምሕርት፣ በማንበብና በመሳሰሉት የምንገበየው እውቀት በእርግጥ አዕምሮን ሊያሰፋ ይችል ይሆናል እንጂ ሕይወትን የሚለውጥ እውቀት አይሆንም። ዳዊት ግን “አውቄዋለሁና” ይለናል። ሙሴም “አውቅህ ዘንድ . . .” እያለ እግዚአብሔርን ሲለምን እናያለን (ዘጸ. 33፥13)። ሮሜ 9፥15-18 ላይ እግዚአብሔር እንደ ተናገረው ከእኛም ሀሳብና ጥበቃ እግዚአብሔር የራሱ የሆነ መለኮታዊ እና ሉዓላዊ ሥራ መፈጸም ይችላል። እግዚአብሔርን በሉዓላዊነቱና በታላቅነቱ  እናውቀዋለን ወይ? ሁሉ ነገር ተስተካክሎ ሳለ ሳይሆን ነገሮች ምስቅልቅል ሲሉ በሉዓላዊነቱ ተማምነን አውቀዋለሁ ማለት እንችላለን ወይ? እኛ ያልነውና የጠበቅነው ሳይሆን ቀርቶ ነገሮች ባልጠበቅነው ነገር ቢሄዱ ለሉዓላዊነቱና ታላቅነቱ እውቅና ሰጥተን በእርሱ ተማምነን እናርፋለን ወይ? ዳዊት እግዚብሔርን ከማወቁና በእርሱም ከማረፉ የተነሳ የእግዚአብሔርን ሉዓላዊነት በማወጅ “በሰማይና በምድር በባሕርና በጥልቆች ሁሉ፥ እግዚአብሔር የወደደውን ሁሉ አደረገ” ይላል።  እርስዎስ?

“ዕረፉ፥እኔም አምላክ እንደ ሆንሁ እወቁ በአሕዛብ ዘንድ ከፍ ከፍ እላለሁ፥ በምድርም ላይ ከፍ ከፍ እላለሁ” መዝ. 46፥10

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *