“ኢዮሣፍጥም ፈራ፥ እግዚአብሔርንም ሊፈልግ ፊቱን አቀና በይሁዳም ሁሉ ጾም አወጀ” (2ዜና 20፥3)
በዚህ ክፍል ኢዮሳፍጥ በሦስት ጠላት ነገሥታት መከበቡን እናያለን። የሞዓብና የአሞን ልጆች ከምዑናውያን ጋር ኢዮሣፍጥን ሊወጉ መሰለፋቸውን ለኢዮሳፍጥ ወሬ ደረሰው ይላል። ኢዮሳፍጥም ሰው ነውና እንኳን ሦስት ጠላት አንድ ጠላትም ቢሆን ቀላል አይደለምና “ፈራ” ይላል። ሌላ ሰው ይህን የመሰለ ከበባ ቢገጥመው ሲፈራ ብሎም ብዙ ሊፍጨረጨርና ብዙ ዓይነት የግልና የወል መፍትሄ አዘል ሙከራዎች ማድረጉ አይቀርም። ኢዮሳፍጥ ግን መንፈሳዊ ሰው ነው፤ እንደ ሰው ቢፈራም እንኳ የእግዚአብሔር ሰው ነውና ለጥያቄ ሁሉ መፍትሄ ያለውን አምላኩን እግዚአብሔርን “ሊፈልግ ፊቱን አቀና” ይላል። ይህ ብቻም አይደለም “በይሁዳ ሁሉ ጾም አወጀ” ይላል።
እስራኤል ከግብጽ ሲወጡ የፈርዖንን ኃይል የሚቋቋም ሌላ ምድራዊ ወታደራዊ ኃይልና አሠራር አልነበራቸውም። ኃይላቸውና ታዳጊያቸው እግዚአብሔር ብቻውን ነበር። እግዚአብሔር ከግብጽ ሲያወጣቸውና የተጓዙት ጉዞ ሁሉ ተአምራዊ አሠራሩ ያለበት፣ ኑሮአቸውም ሆነ አመጋገባቸው ሁሉ በእግዚአብሔር ስንቅ የተሞላ ነበር። በኢዮሳፍጥም ጉዳይ ሦስቱን ጠላት ነገሥታት የሚቋቋም በቂ ወታደራዊ ኃይልና ዝግጅት አልነበረም። ነገር ግን ያ አማላካቸው እግዚአብሔር እንደ ወትሮው ሊረዳቸው ይችላልና ኢዮሳፍጥ በጾምና በጸሎት እግዚአብሔር መፈለግ ጀመረ።
ለክርስትና ጉዞ ሊሚጠቅሙ ከሚችሉ ብዙ ሀሳቦች መካከል እነዚህን ሁለቱን ልብ ይበሉ፦ እግዚአብሔርን መፈለግና ጸምን ማወጅ። ከእግዚአብሔር ፈቃድ ግራቀኝ ማለት ጉዞአችንን ዓላማ ቢስ ሊያደርገው ይችላል፤ ከነዓን የሚለው ዓላማ ጠፍቶ አርባ ዓመት መንከራተት ሊሆን ይችላል። ስለሆነም ይህ እንዳይሆንብንና ውጤትና ዓላማ ያለውን የ|ሕይወት ጉዞ ለመጓዝ እንድንችል እግዚአብሔርን መፈለግ፣ አካሄዳችንን ማስተካከልና ከእግዚአብሔር ጋር መጣበቅ ያስፈልገናል።
በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ውስጥ ጾምና ጸሎት በታወጀበት ጊዜ ሁሉ አስደናቂ ታሪክ የተሰራበት፣ አስደናቂ ውጤት የተገኘበትና እግዚአብሔር የከበረበት ሁኔታ እናያለን። በማኅበራዊ ብቻ ሳይሆን በግልም ቢሆን በጾምና በጸሎት የቆየንበት ጊዜ በጣም አስደናቂ ውጤት ያገኘንበት ነው። በአስቴር ዘመን ሊቆረጥ የነበረው የእስራኤል ታሪክ እንደገና የተቀጠለበት፣ ጠላትም ያፈረበት በጾምና በጸሎት ነበር። ሌላ ቀርቶ አሕዛብ (ዓለማውያን) የሆኑት የነነዌ ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት በጾሙ ጊዜ ታሪካቸው ተለውጧል። ዛሬም ማስተዋል ያጣንበት ጉዳይ፣ ድንግዝግዝ ያለብን ነገር ቢኖር በጾምና ጸሎት በእግዚአብሔር ፊት እንቆይ፣ መፍትሔም እናገኛለን።