የጥሞና ቃል ክፍል 26

“ኑ፥ በእግዚአብሔር ደስ ይበለን ለአምላክ ለመድኃኒታችን እልል እንበል”

መዝ. 95፥1

ቅዱስ ዳዊት “ኑ፥ በእግዚአብሔር ደስ ይበለን!” የሚል ጥሪ አቅርቦአል። እንደ ገናም “ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ ሲሉኝ ደስ አለ” ይላል። ቅዱስ ጳውሎስም “ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፣ ደግሜ እላለሁ፥ ደስ ይበላችሁ” (ፊል. 4፥4) ይላል። ብዙ መከራና ውጣ ውረድ ባለበት ዓለም፣ በየቀኑ ተግዳሮት በበዛበት ዓለም እንዲት ብሎ ሁሌ ደስ ሊለን ይችላል? በየቀኑ የሚቆረቍረን ነገር የለም ወይ? ተግዳሮቶች የሉብንም ወይ? በየቀኑ ሠልፍ የለብንም ወይ?

ኢዮብ “በምድር ላይ የሰው ሕይወት ብርቱ ሰልፍ አይደለምን?” (7፥1) እንዳለው ብዙ ሰልፍ አለ። በብዙ ውጊያና መከራ ልናልፍ እንችላለን። ነገር ግን የደስታችን ምንጭ በሚለዋወጠው ዓለም ወይም ግዑዝ በሆነ ጊዜያዊ ነገር ሳይሆን በዘላለማዊውና በማይለወጠው በራሱ በአምላካችን በእግዚአብሔር ማድረግ እንዳለብን ነው። ሁልጊዜ ደስ ሊለን የሚችለው ልባችን በእርሱ ሲያርፍ ነው። ዕንባቆምም በሁኔታዎች የታወከበት ጊዜ ነበር። በመጨረሻ ግን እግዚአብሔር ውስጡንና እይታውን ስለፈወሰ “ምንም እንኳ” በሚል ሐረግ የጎደሉትን ሁሉ ዘርዝሮ እርሱ ግን ዓይኑን ከሁኔታዎች አንስቶ “በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል” አለ።

“ምንም እንኳ በለስም ባታፈራ፥ በወይንም ሐረግ ፍሬ ባይገኝ፥ የወይራ ሥራ ቢጐድል፥ እርሾችም መብልን ባይሰጡ፥ በጎች ከበረቱ ቢጠፉ፥ ላሞችም በጋጡ ውስጥ ባይገኙ፣ እኔ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል በመድኃኒቴ አምላክ ሐሤት አደርጋለሁ” {ዕን. 3፥17-18)

አልሞላም፣ ጐድሏል . . .የምንለው ነገር ሊኖር ይችላል። የጠፋብን ወይም ያጣነው ነገር ሊኖር ይችላል። ብዙ ተስፋ አድርገነው ያላገኘነው ነገር ሊኖር ይችላል። ጌታ ግን ከሁኔታዎች በላይ ነው። ሁኔታዎች ደስ ባያሰኙንም በእግዚአብሔር ደስ ይበለን!  ጌታም ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ይሠራዋል (መክ. 3፥11)። እስከዚያም “ባንዝልም በጊዜው እናጭዳለንና መልካም ሥራን ለመሥራት አንታክት” (ገላ. 6፥9)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *