የጥሞና ቃል ክፍል 28

“ነገር ግን ቃል ተናገር፥ ብላቴናዬም ይፈወሳል!” (ሉቃስ 7፥7)

ሉቃስ ምዕራፍ ሰባት ብዙ አስደናቂ ታሪኮችን ይዟል። የመጀምሪያው ኢየሱስ ወደ ቅፍርናሆም ሲገባ የተገለጠው የአንድ መቶ አለቃ እምነት ነበር። ይህ መቶ አለቃ የሮማውያንን መንግሥት የሚያገለግል ባለ ሥልጣን ነበር። በዚያን ጊዜ የእስራኤል ምድር ከአንድ መቶ ዓመት ዘመን በላይ በሮማውያን መንግሥት ቅኝ ግዛት ሥር ነበረች። ነገር ግን የመቶ አለቃው ጨካኙን የሮማውያን ገዢ ሥርዓት ለማስጠበቅ የሚያገለግልና ከአህዛብ ወገን የነበረ ቢሆንም በሕዝቡ ዘንድ የሚደነቁ ባህርዮችን አሳይቷል። ከአህዛብ ወገን ሆኖ ነገር ግን ለእስራኤል ሕዝብ ትልቅ ፍቅር ነበረው፣ ከዚህም ፍቅር የተነሳ የሚያመልኩበትና ሃይማኖታዊ ሥርዓታቸውን የሚፈጽሙበት ምኵራብ ራሱ ሰርቶላቸዋል። ስለዚህም መልካም ሥራው የአይሁድ ሽማግሎች መስክረውለታል። ሌላው የሚደነቅበት ጉዳይ ለባርያው የበረው ፍቅር ነው። ከፍቅሩ የተነሳ ባርያው እስከ ሞት ሲታመም ተጨነቀለት።

ከዚህ ይበልጥ የሚያስደንቀው ግን መቶ አለቃው በኢየሱስ ቃል ላይ የነበረው እምነት ነበር። ባርያው ታምሞ ለሞት ሲቃረብ በመጀምሪያ ሽማግሎችን ወደ ኢየሱስ ልኳል። ቀደም ሲል የላካቸው የአይሁድ ሽማግሎች ባቀረቡት ልመና መሠረት ኢየሱስ ወደ ቤቱ አቅጣጫ እየተጓዘ ነበር። ወደ ቤቱ በተቃረበ ጊዜ ግን የመቶ አለቃው ሌሎች ወዳጆቹን ልኮ “ጌታ ሆይ በቤቴ ጣራ በታች ልትገባ አይገባኝምና አትድከም፣ ስለዚህም ወደ አንተ ልመጣ እንዲገባኝ ሰውነቴን አልቈጠርሁትም፤ ነገር ግን ቃል ተናገር፥ ብላቴናዬም ይፈወሳል” በማለት በኢየሱስ ቃል ሕያውነትና ተአምራዊነት ያለውን ጽኑ እምነት ሳይጠራጠር ገለጸ። ኢየሱስም “ይህን ሰምቶ በእርሱ ተደነቀ፥ ዘወርም ብሎ ለተከተሉት ሕዝብ፣ እላችኋለሁ፥ በእስራኤልስ እንኳ እንዲህ ያለ ትልቅ እምነት አላገኘሁም አላቸው”።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *