“ጌታም ባያት ጊዜ አዘነላትና። አታልቅሽ አላት። ቀርቦም ቃሬዛውን ነካ፥ የተሸከሙትም ቆሙ፤ አለውም።
አንተ ጐበዝ፥ እልሃለሁ፥ ተነሣ። የሞተውም ቀና ብሎ ተቀመጠ ሊናገርም ጀመረ፥ ለእናቱም ሰጣት”
(ሉቃስ 7፥13-17)
ጌታ ኢየሱስ በአንድ መቶ አለቃ እምነት እየተደነቀ ከቅፍርናሆም ናይን ወደምትባል ከተማ አመራ። በናይን ከተማም አንድያ ልጇ የሞተባትን ሴት አይቶ አንዳዘነላትና ልጁን ከሞት እንዳስነሳ በዚህ ክፍል ተጠቅሷል። የሞቱትን ስለ ማስነሳት በሚመለከት ከተዘገቡት ሦስቱ ተአምራቶች አንደኛው በዚህ ክፍል ያለው ነው። ሁለተኛው በማር. 5፥22 የተጠቀሰው የኢያኢሮስ ሴት ልጅ ከሞት መነሳት ሲኦህን ሦስተኛው በዮሐ. 11 ላይ የተጠቀሰው የአልአዛር ከሞት መነሳት ነው። በአዲስ ኪዳን የተጠቀሱት እነዚህ ሦስቱ ብቻ ቢሆኑም ብዙ ሊኖሩ እንደሚችሉ ሉቃስ 7፥22 ፍንጭ ይሰጣል።
ታርኩ እንዲህ ነው። አንዲት የናይን ከተማ ኗሪ መበለት አንድያ ልጇ ሞቶ ልትቀብር በከተማው ለቀስተኛ ሕዝብ ታጅባ ወደ መካነ-መቃብር ጉዞ ታመራ ነበር። የሞተውንም ጎበዝ አስከሬን በቃሬዛ የተሸከሙ በህዝቡ ፊት ቀስ ብለው ያዘግማሉ። ብዙ የከተማው ህዝብም ከኋላዋ ይከተላሉ፣ አንድም ቃል ግን አልተነፈሱም። በእርሷና በሕዝቡ ላይ ትልቅ የሐዘን ድባብ ጥላ አርፏልና ሕዝቡ ዝም ብሎ ወደ መቃብር ጉዞ ብቻ ሆነ! ድሮስ ቢሆን ምን ይሉ ኖሯል! እርሷን አጅበው ሀዘኔታቸውን ከመግለጽ በቀር ምን ሊሏት ይችላሉ? ምናልባት “አይዞሽ” ሊሉ ይችሉ ነበር፤ ነገር ግን “አይዞሽ” ብቻውን ምን ይጠቅማታል? አንድ ልጅ ብቻ ነበራት፣ እርሱንም ሞት ቀማት። ሃዘኗ ጥልቅ ነበር፣ ውሽመጧ ተቆርጧል! የወላድ እናት አንጀት በሐዘን እርር ኩምትር ብሏል፤ የሰው አይዞሽ ሊፈውሰው አይችልም። አሁንም ለማልቀስ ኃይል እስክታጣ ድረስ ማልቀሷን ታለቅሳለች፣ የሰቆቃው ለቅሶ፣ እምቧዋም መቆም አልቻለም። ወይኔ ልጄ! እኔው ልሙትልህ! እኔኑ ያርገኝ! አዶናይ ምን በደልኩህ? እኔ ቆሜ ልጄን ልቅበር! ልጄ! አለኝታዬ! የኔ ማር ወለላ! ለወግ-ማዕርግ ደርሰህ ማየት፣ ሠርግህን መደገስ ስጠብቅ፣ ልጅ ወልደህ ልታስታቅፈኝ ሳልም! ምነው ልጄ! ምነው ጨከንህ! ምነው ካድክኝ? ልጄ! ልጄ! እኔ ልሙትልህ! ልጄ! ትጦረኛለህ ብየ ተስፋ ሳደርግ! ለማን ትተኸኝ ትሄዳለህ? እኮ መልስልኝ? ልጄ! ልጄ . . .!
ይህ ቀን ለናይን ከተማ ሕዝብ ከባድ ቀን ነበር፣ የናይን ከተማ ሕዝብ አንገታቸውን ያስደፋ ቀን ነበር። የሐዘን መንፈስ ተጫጭኖአቸው ሴቲቱን አጅበው እንባቸው እየፈሰሰ ወደ መቃብር አቅጣጫ ከከተማው በር ሊወጡ ሲሉ፣ ኢየሱስም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ከተማ ሲገባ በሩ ላይ ተገናኙ። ምን ሆናለች ብሎ አልጠየቀም፣ ቃሬዛው ፊት ለፊት፣ ልጄ እያለች ጉሮሮዋ እስኪሰነጠቅ ድረስ የምታለቅስ እጅግ አሳዛኝና ምስኪን እናት ከኋላ፣ የተጨነቀም ሕዝብ ከእርሷ ኋላ ሲከተሉ፤ ። ሁኔታው ግልጽ ነበር። ጥያቄም መልስም አላስፈለገም። የመበለቲቱ ለቅሶ ልቡን አባባው። ባያት ጊዜ አዘነላትና ርህሩሁ ኢየሱስ ወደ ሴቲቱ ተጠግቶ “አታልቅሽ አላት”።
ቃሬዛውና ኢየሱስ በከተማው በር ተገናኙ፤ ሞትና ሕይወት ፊት ለፊት ተፋጠጡ። ቀደም ሲል ሞት ጉልበተኛ ሆኖ ያንን ጎበዝ ማርኮታል፣ ታድያ አሁን አያ ሞት በኢየሱስ ፊት አቅም ኖሮት ይቆም ይሆን? ኢየሱስም “ቃሬዛውን ነካ፥ የተሸከሙትም ቆሙ፤ አለውም። አንተ ጐበዝ፥ እልሃለሁ፥ ተነሣ። የሞተውም ቀና ብሎ ተቀመጠ ሊናገርም ጀመረ፥ ለእናቱም ሰጣት” ከሞት የተነሳው ጎበዝ “ይናገር ጀመር”። አቤት! ምን ብሎ ይሆን? ነፍሱ ከስጋው በተለየች ጊዜ ከሞት ወዲያ ስላለው ሕይወት ያየውን ተናግሮ ይሆን? ያም ሆነ ይህ – ልጁ ከሞት ተነሥቷል! ለቅሶ ወደ እልልታ ተቀይሯል! ሐዘን በደስታ ተለውጧል! ዝም ብሎ ሬሳውን ያጅብ የነበረው ህዝብ ሆ! እያለ እየዘመረ ወደ ከተማው ተመልሶ ይሆናል። የሃዘን ዳስ የሽብሸባ ዳስ ሆኖ ይሆናል! ልጇ የተነሳላት መበለትስ “ክብሬ ትዘምርልህ ዘንድ ዝምም እንዳትል ልቅሶዬን ለደስታ ለወጥህልኝ፥ ማቄን ቀድደህ ደስታንም አስታጠቅኸኝ” (መዝ. 30፥11) ብላ ይሆን? ስለ መበለቲቱ እምነት የተጻፈ ነገር የለም። ጌታ ያደረገላት ውለታ ስለዘነላት ብቻ ነው።
በርጠሜዎስ “የዳዊት ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ማረኝ እያለ” ሲጮህ “ብዙዎችም ዝም እንዲል ገሠጹት፤ እርሱ ግን፦ የዳዊት ልጅ ሆይ፥ ማረኝ እያለ አብዝቶ ጮኸ። ኢየሱስም ቆመና። ጥሩት አለ” (ማር. 10፥46-49)። ኢየሱስ የሚያለቅሱትን አያልፍም፤ በሃዘንና በመከራ የተጎዱት ሲያለቅሱ ዝም አይልም፤ አይቶ እንዳላየ አይሆንም። በኢያሪኮ የበርጠሜዎን ጩኸት አላለፈም፣ ሰምቶም ዝም አላለም። የእርስዎም ጩኸት ኢየሱስ ይሰማል! ጸሎትዎን ይመልሳል! በሕይወትዎ የተሸከሙት ቃሬዛ ሊኖር ይችላል፤ በእምነትና በትእግስት ጌታን ይጠብቁት!