“ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ!” (ፊል. 1፥27-30)
ክርስቶስ ሕይወት ነው፣ ሕይወትም ኑሮ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ “ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ ሞትም ጥቅም ነው” (ፊል. 1፥21) ብሏል። ወደ ጌታ ስንመጣ ምንም ነገር ከማድረጋችን በፊት አስቀድመን ከእርሱ ጋር መኖር መለማመድ አለብን። ከአገልግሎት በፊት መኖር አስፈላጊ ነው። ከመኖር የተነሳ የምንሰጠው አገልግሎት ፍሬ አለው። “በእኔ ኑሩ እኔም በእናንተ። ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ባይኖር ከራሱ ፍሬ ሊያፈራ እንዳይቻለው፥ እንዲሁ እናንተ ደግሞ በእኔ ባትኖሩ አትችሉም” (ዮሐ. 15፥4)። ጌታም ደቀ መዛሙርቱን ሲጠራ በመጀምሪያ ከእርሱ ጋር እንዲኖሩ ነው። “ወደ ተራራም ወጣ፥ ራሱም የወደዳቸውን ወደ እርሱ ጠራ፥ ወደ እርሱም ሄዱ፤ ከእርሱም ጋር እንዲኖሩና ለመስበክ እንዲልካቸው” (ማር. 3፥13-14)። “ለክርስቶስ እንደሚገባ ኑሩ” የሚለው የሐዋርያው ጳውሎስ አባታዊና ሐዋርያዊ ምክር ነው። እንዴት ነው እንደሚገባ የምኖረው? ከጌታ ጋር መኖር በርግጥ የተመቸ ነው። ነገር ግን ጌታን አስከብረን ከሰው ጋር የመኖር ሁኔታ ግን የተመቸ ላይሆን ይችላል። ብዙ ፈታኝ ነገሮች ሊገጥሙን ይችላሉ። ከሰው ጋር መኖር ቀላል እንዳልሆነ ይታወቃል። አንዳንድ ሰዎች እንዲያውም “አበሾች አብረው መኖር አይችሉም፤ ተለያይተውም መኖር አይችሉም” ሲሉ ይደመጣል። በእርግጥ በአበሻውም ሆነ በሌላው ማኅበረ ሰብ ያለው ሕብረትና አንድነት በተለያዩ ምክንያቶች ከውስጥ ሊቦረቦር፣ ወይም ከውጭ ሊሸረሸር ወይም ሊፈርስም ይችላል። ምክንያቱ የተመሠረተበት ዓላማ ጊዜያዊና ምድራዊ ሊሆን ስለሚችል ነው።
ክርስቶስ ራስ የሆነባት፣ የክርስቶስም አካል የሆነች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለው የቅዱሳን አንድነትና ሕብረት ግን የሚፈርስ አንድነት አይደለም። ምክንያቱ፡ 1ኛ. “የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ” (ኤፌ. 4፥13)። 2ኛ. ታላቅ ዋጋ የተከፈለበት ስለሆነ። 3ኛ. ሰማያዊ ስለሆነ 4ኛ. ዘላለማዊ ስለሆነ ወዘተርፈ . . .። ምናልባት ይህንን አንድነት ለማፍረስ የሚጥር ሰው ቢኖር እንኳ የቅዱሳንን አንድነት ቤተ ክርስቲያንን ከማፍረሱ በፊት እርሱን ራሱን እግዚአብሔር ይፈርሰዋል። “ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፥ ያውም እናንተ ናችሁ” (1ቆሮ. 3፥16-17)።
ስለሆነም ለጌታ የሚገባና ለጌታ የሚመጥን ኑሮ፣ እርሱን የሚገልጥ ሕይወት እንድንኖር ተጠርተናል፣ የእግዚአብሔርም ፈቃዱ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ ያስተላለፋቸው ተመሳሳይ የክርስቲያናዊ ግዴታ ትእዛዛትም አሉ፣ ጥቂቶቹ እነሆ፦ 1ኛ. በአንድ ልብ ስለ ወንጌል ሃይማኖት አብራችሁ ተጋደሉ፣ 2ኛ. በአንድ መንፈስ እንድትቆሙ። ለክርስቶስ መኖር ስንጀምር ተቃዋሚ ይበዛል። ሆኖም ከእነ ነህምያ እንደምንማረው ተቃውሞ ሲበዛ የበለጠ እንበረታለን። ቅዱስ ጳውሎስም ቀጥሎ 3ኛ. በተቃዋሚዎች አትደንግጡ፣ ይህም ሀ. ለእነርሱ የጥፋት ምልክት ለ. ለእኛ ግን የመዳናችን ምልክት እንደሆነ አመልክቷል።
“በተጠራችሁበት መጠራታችሁ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እለምናችኋለሁ፤ በትሕትና ሁሉና በየዋህነት፤
በትዕግሥትም፤ እርስ በርሳችሁ በፍቅር ታገሡ፤ በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ” (ኤፌ. 4፥1-3)
ወንጌል ዋጋ ያስከፍላል! ስለሆነም የሚጠይቀውን ዋጋ እየከፈልን እንደሚገባ መኖር!
እንደሚገባ . . . .ወለም ዘለም ሳትሉ፣ ቸል ሳትሉ፣ ወደ ቀኝም ወደ ግራም ሳትሉ . . . ኑሩ!”