“ነገር ግን . . .”
“የሶርያ ንጉሥ ሠራዊት አለቃ ንዕማንም እግዚአብሔር በእርሱ እጅ ለሶርያ ደኅንነትን ስለ ሰጠ በጌታው ዘንድ ታላቅ ክቡር ሰው ነበረ ደግሞም ጽኑዕ ኃያል ነበረ፥ ነገር ግን ለምጻም ነበረ” (2ነሥ. 5፥1)
በእያንዳንዱ ሰው ሕይወት “ነገር ግን” የሚባል አሉታዊ የመስተጻምር ቃል አለ። ንዕማን ምንም እንኳ ታዋቂና ዝነኛ፣ ሰው “በጌታው ዘንድ ታላቅ ክቡር ሰው . . . ደግሞም ጽኑዕ ኃያል” የነበረ ቢሆንም “ነገር ግን ለምጻም ነበረ” ይላል። ንዕማን የተያዘበት በሽታ እጅግ አስጠሊና የሚፈራ በሽታ ነው። በዚህ ዓይነት አስቀያሚ በሽታ መያዙ ራሱ ከሕዝብ ለመገለል ይዳርገዋል።
በንዕማን ቤት ግን እንደ ሰውኛ መረዳት በምርኮ የመጣች፤ ነገር ግን እግዚአብሔር በዓላማ እዚያ ቤት ያስቀመጣት አንዲት እስራኤላዊት ምርኮኛ “ታናሽ ብላቴና ሴት” በከዳሚነት “የንዕማንንም ሚስት ታገለግል ነበር”። ለንዕማን ዓይን የማትገባ ተራ ምርኮኛ፣ ከዳሚ ሠራተኛ! የሶርያ ጠቢባን ሊፈቱት ያልቻሉትን የንዕማን ደዌ ፈውስ የት እንዳለ የምታውቅ የእግዚአብሔር ስውር አገልጋይ!
ታሪኩ በታናሽ ሰው ምክር ተጀምሮ በሌሎች ታናናሽ ሰዎች ምክር ያልቃል። ልጅቱ እዚያ ቤት ምርኮኛ የቤት ከዳሚት የነበረች ብትሆንም በደረሰባት ግፍና ስቃይ በእነ ንዕማን ቤተ-ሰብ መራራነትንና ጥላቻን አላሳደረችም። ይልቁንስ ለጌታዋ ለንዕማን ርኅራሄ አደረባት፣ አዘነችለት፣ እንዲፈወስ መከረችው። የፈውሱም አቅጣጫ በመላ ነገረችው። “ጌታዬ በሰማርያ ካለው ከነቢዩ ፊት ቢደርስ ኖሮ ከለምጹ በፈወሰው ነበር” ስትል ለእመቤትዋ ሀሳብ አቀረበች። ንዕማንም ይህን የተስፋ ዜና ሲሰማ ልቡ ሞቀ። ወዲያውኑ ወደ ጌታው ወደ ሶርያ ንጉሥ ገባና ይህንን ተስፋ ሰጭ ወሬ ነገረው። የሶርያም ንጉሥ “አሥርም መክሊት ብር፥ ስድስት ሺህም ወርቅ፥ አሥርም መለውጫ ልብስ” ገጸ-በረከት በእጁ አስይዞ ወደ እስራኤል ንጉሥ ሰደደው። የእስራኤል ንጉሥ ግን ይህ በገጸ-በረከት የታጀበ “ይህ የታወቀና የታመነ ጀነራሌ ነው፣ እባክህ እንዲፈወስ ተባበረው” የሚል አደራ አዘል ደብዳቤ ሲቀበል ዱብ ዕዳ ሆኖበት ተበሳጨ። “ደብዳቤውን ባነበበ ጊዜ ልብሱን ቀድዶ፣ ሰውን ከለምጹ እፈውስ ዘንድ ይህ ሰው ወደ እኔ መስደዱ እኔ በውኑ ለመግደልና ለማዳን የምችል አምላክ ሆኜ ነውን? ተመልከቱ፥ የጠብ ምክንያትም እንደሚፈልግብኝ እዩ” ብሎ በቁጣ ነደደ። ፍርሃትና ሥጋት የተደባለቀበት ግራ መጋባት ሰውነቱን ሁሉ ወረረው።
“የእግዚአብሔርም ሰው ኤልሳዕ የእስራኤል ንጉሥ ልብሱን እንደ ቀደደ በሰማ ጊዜ። ልብስህን ለምን ቀደድህ? ወደ እኔ ይምጣ፥ በእስራኤልም ዘንድ ነቢይ እንዳለ ያውቃል ብሎ ወደ ንጉሡ ላከ”
ጀነራል ንዕማንም “በፈረሱና በሰረገላው መጣ፥ በኤልሳዕም ቤት ደጃፍ ውጭ ቆመ”። ኤልሳዕም። ሂድ፥ በዮርዳኖስም ሰባት ጊዜ ታጠብ ሥጋህም ይፈወሳል፥ አንተም ንጹሕ ትሆናለህ ብሎ ወደ እርሱ መልእክተኛ ላከ። ንዕማን ግን ተቈጥቶ ሄደ፥ እንዲህም አለ፦ “እነሆ፥ ወደ እኔ የሚመጣ፥ ቆሞም የአምላኩን የእግዚአብሔርን ስም የሚጠራ፥ የለምጹንም ስፍራ በእጁ ዳስሶ የሚፈውሰኝ መስሎኝ ነበር። የደማስቆ ወንዞች አባናና ፋርፋ ከእስራኤል ውኆች ሁሉ አይሻሉምን? በእነርሱስ ውስጥ መታጠብና መንጻት አይቻለኝም ኖሮአልን? ዘወርም ብሎ ተቈጥቶ ሄደ። ባሪያዎቹም ቀርበው። አባት ሆይ፥ ነቢዩ ታላቅ ነገርስ እንኳ ቢነግርህ ኖሮ ባደረግኸው ነበር ይልቁንስ። ታጠብና ንጹሕ ሁን ቢልህ እንዴት ነዋ! ብለው ተናገሩት”
ጀነራል ንእማን ትዕዛዝ መቀበል አቃተው። ምክንያቱ ጀነራል ነውና ሌሎችን የማዘዝ እንጂ የመታዘዝ ልምድ አልነበረውምና። አንድም በመሰለው የሚመራ ሥጋ ለባሽ ሰው ነበርና “መስሎኝ ነበር” በማለት የእግዚአብሔርን ቃል መታዘዝ አቃተው። በሌላ በኵልም ንዕማን የግትርነት ባሕርይ የተላበሰ ኮስታራና የኔ ሀሳብ ብቻ ብሎ የያዘውን ለመልቀቅ የማይፈቅድ የእምቢዮው ስብእና የተጠናወተው ግትር ሰው ይመስላል።
ዛሬስ ስንቶቻችን ነን “መስሎኝ ነበር” በሚል አባዜ በእግዚአብሔር የመጐብኘታችንን ቀን የምናራዝመው? እንደ ወደደና እንደ ፈቀደ የሚሠራ አምላክ እግዚአብሔር ብቻ ነው። በዚህ መንገድ ብቻ ብለን እግዚአብሔርን የምንወስነው እኛ ማን ነን? ጀነራል ንዕማን ያንን ሁሉ ጉዞ ዋጋ ከፍሎ መጥቶ ከፈውሱ ጋር ፊት ለፊት ሲገናኝ በግትርቱ ምክንያት ፈውሱ ለጥቂት አምልጦት ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔር ምሕረት አበዛለት፣ በታናናሾች በኩል የመጣውን የእግዚአብሔር ምክር ተቀብሎ የተባለውን ሲቀበል ተፈወሰ። ከተፈወሰ በኋላ ንዕማን “መስሎኝ ነበር” ከሚል ጭፍን ሃይማኖታዊ ምክንያት ወጣ። “ከጭፍራው ሁሉ ጋር ወደ እግዚአብሔር ሰው (ኤልሳዕ) ተመለሰ፥ ወጥቶም በፊቱ ቆመና። እነሆ፥ ከእስራኤል ዘንድ በቀር በምድር ሁሉ አምላክ እንደሌለ አወቅሁ” ብሎ መሠከረ (ቍ. 15)። የንዕማን ምሥክርነት እግዚአብሔር ሲፈውሰው ሥጋውን ብቻ ሳይሆን መንፈሱንም ጭምር እንደ ፈወሰው ያሳያል።
የእግዚአብሔር አሠራር ይደንቃል። ብዙ ጊዜ የሚሠራውም ዓይናችን በማይገቡ ትንንሽ ሰዎች እንደሆነ ታሪኩ ያሳየናል። ይህን ባለመረዳት ግን ዛሬም አንዳንድ ሰዎች ፓስተር እከሌ ቢጸልይልኝ? ሐዋርያ እግሌ እጁ ቢጭንብኝ ከችግሬ እላቀቅ ነበር ሲሉ ይደመጣል። የእግዚአብሔር ቃል ግን “ትፈወሱም ዘንድ እያንዳንዱ ስለ ሌላው ይጸልይ፤ የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች” (ያዕ. 5፥16)፤ “ከእናንተ እያንዳንዱ የአንዱን ሸክም ይሸከም እንዲሁም የክርስቶስን ሕግ ፈጽሙ” (ገላ. 6፥2)፤ “በሁሉም ላይ ታላቅ ጸጋ ነበረባቸው” (ሐ.ሥ. 2፥42-45) ይላል። እነዚህ ጥቅሶች ሁሉ የሚያሳዩት ክርስቶስ ለአካሉ በቤተ ክርስቲያን የሰጠው ጸጋ እንዳለ፣ የዚያ ጸጋ ተጠቃሚዎች ለመሆንም ዓይናችንን ከሥጋ-ለባሽ ማንሳት እንደሚገባን፤ እግዚአብሔር በታናናሾችም መሥራት እንደሚችል አምነን ፈውሳችንን ከእግዚአብሔር መጠበቅ እንደሚገባን ነው።
“ስለዚህ፥ ከሰማያዊው ጥሪ ተካፋዮች የሆናችሁ ቅዱሳን ወንድሞች ሆይ፥ የሃይማኖታችንን ሐዋርያና ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስን ተመልከቱ!” (ዕብ. 3፥1)