የጥሞና ቃል ክፍል 33

“ኢያሱም ማልዶ ተነሣ፥ እርሱና የእስራኤልም ልጆች ሁሉ ከሰጢም ተነሥተው ወደ ዮርዳኖስ መጡ ሳይሻገሩም በዚያ አደሩ” ኢያሱ 3፥1

ዮርዳኖስን ለመሻገር የሚዘጋጅ ሰው ማልዶ መነሳት አለበት። ይህ ደግሞ የጸሎት ሕይወታችንን ያሳያል። የሚጸልይ ሰው ይሻገራል። የጸሎት ሰው በምንም ዓይነት መከራ ውስጥ ቢያልፍም ይሻገራል። ዳንኤል በየቀኑ ሦስት ጊዜ በአምላኩ ፊት ይጸልይ ነበር። በአድመኞች ሴራ እርሱን ለማጥፋት የተቀነባበረ አዋጅ በጽሑፍ መውጣቱን ሲሰማም “ወደ ቤቱ ገባ የእልፍኙም መስኮቶች ወደ ኢየሩሳሌም አንጻር ተከፍተው ነበር። ቀድሞም ያደርግ እንደ ነበረ በየዕለቱ ሦስት ጊዜ በጕልበቱ ተንበርክኮ በአምላኩ ፊት ጸለየ አመሰገነም” (ዳን. 6፥10)። ከአንበሶችም አፍ አመለጠ፤ ንጉሡ ሊያድነው ሞክሮ ነበር። ነገረግን አልሆነም። በአንበሳ ጉድጓድ ተጣለ። የእኛም ነገሮች ያሉት በእግዚአብሔር እጅ እንጂ በሰዎች አይደለም። ከዚያም በአንበሳ ጉድጓድ ውስጥ ሆኖ እርሱ በሰላም ነበር፤ ነገር ግን ንጉሡ እንቅልፍ አጥቶ ነበር። እግዚአብሔር በጸሎት ለእኛ ሰላም ይሰጣል፤ ስለ እኛ ደግሞ ሌሎች ሰዎችን እንቅልፍና ዕረፍት ይነሳል።

ዮርዳኖስን ለመሻገር በእምነት መውጣት ነበረባቸው። ያንን የፈሩትንና ሞላ የተባለውን ባሕር በእምነት መርገጥ ነበረባቸው። ዛሬ እኛም ግዙፍ የመሰለንና እምነታችንን የሚፈትን ነገር የእግአብሔርን ቃል ይዘን በእምነት ችግሮቻችንን መርገጥ ይኖርብናል። ሰይጣን ሁልጊዜ የእኛን ሞትና ጥፋት ነው የሚናገረው። ድምጹን ሰምተን ካስተናገድነውም ሞት ሊታየን ይችላል። ጠላት ሊውጠን ያሰፈስፋል፤ የእግዚአብሒር ቃል ግን ስለ ጠላታችን ስለ ዲያብሎስ  “ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና” ይላል። ሆኖም ዲያብሎስ “እንደ” አንበሳ ነው የተባለው እንጂ አንበሳ ነው አልተባለም። ብቻውን ተአምር የሚያደርግ የይሁዳ አንበሳ የተባለው የናዝሬቱ ኢየሱስ ብቻ ነው። ስለዚህ እርሱ በሰጠን ስልጣን የጠላትን ድምጽ በርትተን በጸሎት መዋጋት እንጂ ተዘልለን ሞትን መጠበቅ የለብንም።

ዮርዳኖስን ለመሻገር በዮርዳኖስ ላይ የእግዚአብሔርን ተስፋ ቃል ትንቢት መናገር ነበረባቸው። “ዛሬ እግዚአብሔር በመካከላችሁ ድንቅ ነገር ያደርጋል” የሚለው ትንቢታዊ የተስፋ ቃል በእምነት ማወጅ፣ መናገር፣ መውጣት ነበረባቸው። ይህም ማለት ከፊታቸው ስላለው ስለ ዮርዳኖስ መሙላት፣ መከራና ፈተና ማውራትም ማሰብም አልነበረባቸውም። እኛም ዛሬ ስለ ጠላታችን ትልቅነት፣ ድል፣ ብልጠትና ዘዴ ማውራት የለብንም። ስለ ጐልያድ ትልቅነት ሳይሆን ስለ እግዚአብሔር ታላቅነት ብቻ መሆን ይገባዋል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *