የጥሞና ቃል ክፍል 35

“አቤቱ፥ በሕዝብም ፊት በወጣህ ጊዜ፥ በምድረ በዳም ባለፍህ ጊዜ፥ ምድር ተናወጠች፣ ከሲና አምላክ ፊት፥ ከእስራኤል አምላክ ፊት ሰማያትም አንጠበጠቡ” (መዝ. 68፥7-8)

እግዚአብሔር በሕዝቡ ፊት ሲወጣ የሚሆኑ ነገሮች እንመለከታለን። በተራራ ይሁን በሸለቆ የእግዚአብሔር ሕዝብ በሚገኝበት ሁኔታ ሁሉ እግዚአብሔር ይወጣል። ለምን ይወጣል? ሕዝቡን ስለሚወድ የቃል ኪዳን ሕዝቡን እየፈለገ ይወጣል፤ እግዚአብሔር ሲወጣ፦

  1. የእግዚአብሔር ህዝብ ድል ይጎናጸፋል፣
  2. የእግዚአብሔር ሕዝብ ሞገስና ሰማያዊ ውበት ይቀበላል፣
  3. ምርኮ ይመለሳል፣ በለቅሶ ፋንታ የደስታ ዘይት ይቀባል፣
  4. በኃዘንም መንፈስ ፋንታ የምስጋናን መጎናጸፍያ ይደርባል፣
  5. ተራሮች ደልዳላ ሜዳ ይሆናሉ፣ የናስ ደጆች ይሰበራሉ፣
  6. እስራት ይበጠሳል፣ ቀንበርም ይሰበራል፣
  7. ታሪክ ይቀየራል፣ ምስክርነቱንና አሻራውንም ለትውልድ የሚተላለፍ ይሆናል

እግዚአብሔር ከእኛ ጋር እንዲወጣ ከእኛ የሚፈልገው ምንድነው?

ሀ. ቅድስና         ለ. ቃሉን መታዘዝ           ሐ. በእውነትና በመንፈስ ማምለክ    መ. በእምነት መኖር፣

እግዚአብሔር ከፊታችን ሲወጣ ምድር ብቻ ሳትሆን ሰውንም ያናውጣል። ያለ እርሱ ፈቃድ የያዝነውን ነገር ለማስለቀቅና ለማስጣልያ ሊያናውጠን ይችላል። ሰማያት ሲያንጠበጥቡ እንድናይ አሁንም የኛ ነገር ያናውጠው። ከመናወጥ በኋላ ወደሚንጠባጠብ በረከት እንገባለን። ዳዊት “ሥርዓትህን እማር ዘንድ ያስጨነቅኸኝ መልካም ሆነልኝ” እንዳለ እንዲሁ ከመናወጥና ከመጨነቅ በኋላ ዓላማው ገብቶን ጌታን የምናመሰግንበት ምክንያት ይሆንልናል (መዝ. 119፥71)። እግዚአብሔር በፊታችን ሲወጣ እንለወጣለን። የእግዚአብሔር ከእኛ ጋር መውጣት ወሳኝ መሆኑ ሲገባን ብቻ እንደ ሙሴ “አንተ ከእኛ ጋር ካልወጣህስ፥ ከዚህ አታውጣን” እንላለን (ዘጸ. 33፥15)። ቀጥሎም “በምድርም ፊት ካለው ሕዝብ ሁሉ እኔና ሕዝብህ የተለየን እንሆን ዘንድ አንተ ከእኛ ጋር ካልወጣህ፥ እኔና ሕዝብህ በአንተ ዘንድ ሞገስ ማግኘታችን በምን ይታወቃል?” አለ። በአዲሱ ትርጉም “ሀልዎትህ ከእኛ ጋር ካልሄደ ከዚህ አትስደደን። አንተ ከእኛ ጋር ካልሄድህ፣ አንተ በእኔና በሕዝብህ መደሰትህን ሌላው እንዴት ያውቃል? እኔንና ሕዝብህንስ በገጸ ምድር ከሚገኙት ከሌሎች ሕዝቦች ሁሉ ልዩ የሚያደርገን ሌላ ምን አለ?” ይላል። በሌላ አባባል እኛን ከሌላው የሚለየን የእግዚአብሔር ከእኛ ጋር መሆን ነው፣ የእግዚአብሔር ከፊታችን መውጣት ነው። በብሉይ ኪዳን እስራኤልን ከሌላው አህዛብ ልዩ ያደረጋቸው የእርሱ ከእነርሱ ጋር መሆን ነበር። ከእነርሱ ጋር ሲሆን በድል ይጓዛሉ፤ ጠላቶቻቸው ከፊታቸው መቆም አይችሉም። ስለዚህም “አምላክህ እግዚአብሔር እርሱ በፊትህ ያልፋል እርሱ እነዚህን አሕዛብ ከፊትህ ያጠፋቸዋል ትወርሳቸውማለህ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረ ኢያሱ በፊትህ ይሻገራል” (ዘዳ. 31፥3) ተብሎ ተጻፈ። አዎን! አኛ ልዩ የምንሆነው እርሱ ከእኛ ጋር ሲሆን፣ ከፊታችን ሲወጣ ብቻ ነው። ስለዚህም ዛሬ ይህንን ካነበቡ በኋላ እግዚአብሔር ወደሚንጠባጠበው በረከት እንዲያስገባዎትና ሁልዎቱም ከእርስዎ ጋር እንዲወጣ ይጸልዩ፤ በእግዚአብሔር ፊት ጊዜ ይውሰዱ! ወገኔ ሆይ! ያለ እግዚአብሔር ብቻችን የወጣንበት ጊዜ ዛሬ ያብቃ፣ እግዚአብሔር ሲወጣ ብቻ እንውጣ! የምንተኛበት ጊዜ አብቅቶ እግዚአብሔርን አስቀድመን መውጣትና ከእግዚአብሔር ጋር እንድሮጥ በጸጋው ይርዳን! አሜን!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *