የጥሞና ቃል ክፍል 36

“ሕዝቡም የእግዚአብሔርን ቃል እየሰሙ ሲያስጠብቡት ሳሉ፥ እርሱ ራሱ በጌንሳሬጥ ባሕር ዳር ቆሞ ነበር፤ በባሕር ዳርም ቆመው የነበሩትን ሁለት ታንኳዎች አየ፤ ዓሣ አጥማጆች ግን ከእነርሱ ውስጥ ወጥተው መረቦቻቸውን ያጥቡ ነበር። ከታንኳዎቹም የስምዖን ወደ ነበረች ወደ አንዲቱ ገብቶ ከምድር ጥቂት ፈቀቅ እንዲያደርጋት ለመነው፤ በታንኳይቱም ተቀምጦ ሕዝቡን ያስተምር ነበር። ነገሩንም ከጨረሰ በኋላ፥ ስምዖንን። ወደ ጥልቁ ፈቀቅ በል መረቦቻችሁንም ለማጥመድ ጣሉ አለው። ስምዖንም መልሶ፦ አቤቱ፥ ሌሊቱን ሁሉ አድረን ስንደክም ምንም አልያዝንም፤ ነገር ግን በቃልህ መረቦቹን እጥላለሁ አለው። ይህንም ባደረጉ ጊዜ እጅግ ብዙ ዓሣ ያዙ፤ መረቦቻቸውም ተቀደዱ። በሌላ ታንኳም የነበሩትን ጓደኞቻቸውን መጥተው እንዲያግዙአቸው ጠቀሱ፤ መጥተውም ሁለቱ ታንኳዎች እስኪሰጥሙ ድረስ ሞሉአቸው። ስምዖን ጴጥሮስ ግን ባየ ጊዜ በኢየሱስ ጕልበት ላይ ወድቆ። ጌታ ሆይ፥ እኔ ኃጢአተኛ ነኝና ከኔ ተለይ አለው። ስላጠመዱት ዓሣ እርሱ ከእርሱ ጋርም የነበሩ ሁሉ ተደንቀዋልና፤ እንዲሁም ደግሞ የስምዖን ባልንጀሮች የነበሩ የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስም ተደነቁ። ኢየሱስም ስምዖንን። አትፍራ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሰውን የምታጠምድ ትሆናለህ አለው። ታንኳዎችንም ወደ ምድር አድርሰው ሁሉን ትተው ተከተሉት

 

በዚህ ክፍል ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዓሣ አጥማጆች ወደሚገኙበት ሠፈር እንደመጣ እናያለን። ጌታ በተገኘበት ሕይወት፣ ቤት፣ መንደርና ሥፍራ ሁሉ ለውጥ አለ፣ ተአምራት አለ፣ ጌታ ብቻ ይገኝ እንጂ የሚሆን ነገር አለ። በመጀመሪያ ታንኳይቱ ከምድር ጥቂት ፈቀቅ እንድትል “ለመነው” ይላል።  የጨዋነቱ ሁኔታ እዚህ ኵልል ብሎ ይታያል፤ የጌቶች ጌታ ሆኖ ከማዘዝ ይልቅ “መለመነን” መምረጡ የሚያስገርም ትሕትና!

 

በታንኳ ሆኖ ሕዝቡን ማስተማሩን ከፈጸመ በኋላ “ወደ ጥልቁ ፈቀቅ” እንዲሉና መረቦቻቸውን እንዲጥሉ ነገራቸው። እነ ስምዖን ጴጥሮስም እውነታውን መልሰው ነገሩት “አቤቱ፥ ሌሊቱን ሁሉ አድረን ስንደክም ምንም አልያዝንም፤ ነገር ግን በቃልህ መረቦቹን እጥላለሁ አለው። ይህንም ባደረጉ ጊዜ እጅግ ብዙ ዓሣ ያዙ፤ መረቦቻቸውም ተቀደዱ። በሌላ ታንኳም የነበሩትን ጓደኞቻቸውን መጥተው እንዲያግዙአቸው ጠቀሱ፤ መጥተውም ሁለቱ ታንኳዎች እስኪሰጥሙ ድረስ ሞሉአቸው” ይላል። ያም ተአምራት የሕይወት፣ የአቅጣጫ መለወጥ ምክንያት ሆነ፣ ከዓሣ አጥማጅነት ወደ ሰው አጥማጅነት የተሸጋገሩበት ሰዓት ሆነ! ታሪኩ እንደዚሁ ብዙ ሊወጣው የሚችልና ከሕይወት ጋር በማዛመድ ብዙ ትምሕርት የሚገኝበት ቃል የያዘ ነው። ነገር ግን ይህ የጥሞና ቃል (ዲቮሽናል) ስለሆነ ለማሳጠር ያህል ከላይ ያለውን ምንባብ በጽሞናና በማስተዋል እንዲያነቡት እጠይቃለሁ።

 

በዚህ ክፍል ሰባት ነጥቦችን አይተን ከሕይውታችን ጋር እንዴት እንደሚዛመዱ እንመልከት።

 

  1. ጌታ ወደ አጥማጆቹ የመጣበት ጊዜ
  2. ሥራ የፈቱበት – የመረብ ማጠብ ጊዜ
  3. የተስፋ መቍረጥ ጊዜ
  • ባዶ የሆኑበት ጊዜ
  1. የደከሙበት ጊዜ

 

  1. ጌታ ባዶ ወደ ነበረችው ታንኳ መግባቱ፣
  2. ነገራችን ሁሉ ባዶ ሲሆን ጌታ ይገባል፣
  3. ባዶዉን ነገራችንን ጌታ ይገባና በሀልዎቱ ይሞላዋል፣ ይጠቀምብናል፣ ይገለገልብናል፣

 

  1. አገልግሎቱን ከጨረሰ በኋላ ባዶዋን እንዳልተዋት፣
  • ጌታ ከተጠቀመብን በኋላ እንዲሁ ባዶአችንን እንዲሁ አይተወንም፣
  • ሰው ተጠቅሞ ይጥላል፣ ጌታ ቢጠቀምብን ግን ሽልማት አለው። ለጊዜው የከሠርን ቢበምለን እንኳ፣ እርሱ በእጥፍ ይክሰናል፣ ጌታ ግን ይባርከናል።

 

  1. ሌሎች ታንኳዎች እያሉ የስምኦን ወደሆነችው ታንኳ መግባቱ።

በዚያ ቦታ ብዙ ታንኳዎች ይኖራሉ፣ በተለይ ደግሞ በክፍሉ የተጠቀሱ ሁለት ታንኳዎች ነበሩ። ጌታ ኢየሱስ ግን የስምዖን ወደ ሆነችው ገባ፤ ለምን? ብዙ ታንኳዎች እያሉ ለምን ወደ ስምዖን ታንኳ ገባ?

 

በተነጻጻሪነት ወደ አንተ/አንቺ/ እኔስ ሕይወት ለምን ገባ? በዚህ ዓለም ብዙ ጠቢባንና ባለጸጎች እያሉ ለምን ወደ እኛ ሕይወት ገባ? ከእኛ የተሻሉ ሌሎች ብዙ እያሉ ለምን እኛን መረጠ? መልሱ- የጸጋውና ምሕረቱ ምርጫ!

 

  1. የጴጥሮስ የግል ምላሽ፦ ጴጥሮስ ይህንን ሲያይ “በኢየሱስ ጉልበት ወድቆ ጌታ ሆይ እኔ ኃጢአተኛ ነኝና ከእኔ ተለይ” አለ። እኛነታችንን፣ ኃጢአተኝነታችንና ውድቀታችንን ማየት የምንችለው ጌታ ወደ እኛ ሲገባ፣ ብርሃኑ በጨለማው ሕይወታችን ሲበራ ብቻ መሆኑን ያስተምረናል።

 

  1. የሌሎች ቀዳሚ የጋራ ምላሽ – “ተደነቁ”። ጌታ ወደ ሕይወታችን፣ ትዳራችን፣ ኑሮአችን፣ አገልግሎታችን፣ የሥራ ቦታችን ሲገባ በመደነቅ ይሞላናል።

 

  1. ቀጣዩ የጋራ ምላሽ – መደነቅ ብቻ ሳይሆን፡ -“ሁሉን ትተው ተከተሉት”

 

ጌታ ወደ እነ ጴጥሮስ ታንኳ ገብቶ ባደረገው ተአምራት መደነቅ ብቻ ሳይሆን የሕይወታቸውን አቅጣጫ አስቀየራቸው፣ ዓላማ ሰጥቶ በዓላማ ለዓላማ የሚኖሩ ሰዎች አደረጋቸው።

 

በእኛስ ሕይወት እውነት አይደለምን? ጌታ ወደ ታንኳችን፣ ወደ ሕይወታችን፣ ወደ ቤታችን፣ ወደ ኑሮአችን ሲገባ መቅበዝበዝ አበቃ፣ ወድያና ወዲህ መንጠራውዝና መፍገምገም አበቃ! በሰላም ወጥተን የምንገባ የሰላም ሰዎች ሆንን፣ ቀጥ ብለን ቆምን፣ አካሄዳችን ያማረ ሆነ፣ መዓዛችንም ተለወጠ። ለሕይወት ጉዞ አቅጣጫና መዳረሻ አገኘን! የዓላማ ሰዎችም ሆነናል። ጌታ ወደ ታንኳችን (ሁኔታችን) ሲገባ አቅጣጫችንን ያስቀይራል፣ አገልግሎታችንን ይለውጣል።

 

ያለ ጌታ ሕይወት ትርጉም አይኖረውም፤ ጌታ የሌለበት ነገር ሁሉ ባዶ ነው፣ እርካታ የለውም፣ ዓላማ የለውም። ያለ ጌታ የሰበስበነውና እርሱ የማይከብርበት ሁሉ ጌታ ወደ ሕይወታችን ሲገባ ያስጥለናል፣ ያስተወናል፣ በምትኩም የከበረ ወንጌል፣ የከበረ ሕይወት፣ የከበረ ዘላለማዊ ዓላማ ይሰጠናል።

 

ዛሬስ ባዶ ነኝ ያሉበት ነገር በሕይወትዎ ይኖር ይሆን? በሕይወትዎ ክፍተት አለን? ጌታን “ና ወደ ባዶነቴ ግባ” ብለው ይጸልዩ፣ ይለምኑት፣ ይጋብዙት!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *