“እኔ ላደርገው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር አከበርሁህ” (ዮሐ. 17፥4)
ይህንን ቃል ሳነበው እጅግ አስገረመኝ። ጌታ ኢየሱስ በአገልግሎቱ ሁለት ነገሮችን እንዳደረገ ያሳያል። 1ኛ እግዚአብሔር አብ የሰጠውን ሥራ “ፈጸምኩ” ይላል። 2ኛው “አከበርኩህ” ይላል። በሕይወታችን ዘመን እግዚአብሔር የሰጠን ሥራዎች አሉ። በእርግጥ ደህንነታችን የተመሠረተው መንፈሳዊ ሥራን በመሥራት አይደለም፣ ሰው የሚድነው በእምነት በጸጋው ነውና። ይህም ደኅንነታችን በእኛ ሥራ ሳይሆን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በሠራልን ሥራ የተመሠረተና ሙሉ ዋስትና ያለው ነው።
ነገር ግን እምነታችን (ማመናችን) በሥራ መገለጥ ይገባዋል (ኤፌ. 2፥10)። ከዳንን በኋላም እንድናገለግለው ተጠርተናል። ስለሆነም አንዳንዶቻችን በጸሎት አገልግሎት እናገለግላለን፤ ሌሎቻችንም በስብከት፣ በማስተማር፣ በመመስከር፣ ድሆችን በመርዳት ወዘተ እናገለግላለን። በዚህ ሁሉ እንደተቀበልነው ጸጋ በዚህ ምድር እየተመላለስን ጌታን ስናገለግል አብ ይከብራል።
ነገር ግን በአንድም በሌላም መንገድ አገልግሎታችን እንዳንፈጽም አብን እንዳናከብር የሚዋጋን ኃይል እንዳለ ደግሞ አንርሳ። ይህም የዚህ ዓለም የጨለማ ኃይል ሰይጣን ነው። ሰይጣን በሥጋና በደም፣ በዓለምም በኵል ሁሌ ይዋጋናል። እኛም ከሚገጥመን መንፈሳዊ ውጊያ የተነሳ ልንደክም፣ ልንዝል ወይም ቸል ልንል እንችላለን። ደከመን ብለን ወይ የእግዚአብሔር ሥራ መሥራት እናቆማለን ወይም በቸልታ እናገለግላለን ማለት ነው። እግዚአብሔር ግን ቸልተኝነትን ፈጽሞ ይጠላል። እንዲያውም ቸልተኝነት እርግማን እንደሆነ ይናገራል “የእግዚአብሔርን ሥራ በቸልታ የሚያደግ ርጉም ይሁን” (ኤር. 48፥10) ይላል። የተሰጠንን ሥራ እስከፍጻሜ አድርሰን አብን የምናከብርበት እንዲሆን ጌታ ይርዳን።
ወንድሜ ሆይ! ጌታ የሰጠህና አንተ ግን አቋርጠህ የተውከው ነገር አለ? እህቴ ሆይ! ጌታ የሰጠሽና ጀምረህ የተውሽው አገልግሎት አለ? ከጌታ ወደ ተሰጠህ ሥራ ተመለስ! ተመለሺ!
እግዚአብሔር አብ የሰጠህን ሥራ ፈጽም! ጌታ የሰጠሽን ሥራ ፈጽሚ!
የተሰጠን ሩጫ ስንፈጽም ብቻ አብ ይከብራል!