የጥሞና ቃል ክፍል 39

“በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ ለጥቂት ጊዜ መከራን ከተቀበላችሁ በኋላ ራሱ ፍጹማን ያደርጋችኋል ያጸናችሁማል ያበረታችሁማል”

(1ጴጥ. 5፥10)

በዚህ ቃል ውስጥ እግዚአብሔር ወደ ዘላለም ክብሩ እንደጠራን፣ የዚህ የመጠራታችን ዋና መሠረትም ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ሆነ እንመለከታለን። ሌላው እውነት ደግሞ ወደ ዘላለም ክብር የተጠራን ሆነን ሳለ እንኳ ለጥቂት ጊዜ መከራን ልንቀበል እንደምንችል ያሳያል። ሆኖም በዚህ ቃል ውስጥ “አምላክ” ከሚለው ቃል በፊት የተጻፈውን ቅጽል ሐረግ ልብ እንበል፦ “የጸጋ ሁሉ አምላክ” ይለዋል። የምን? “የጸጋ ሁሉ”! ይህ እውነት ማለትም አምላካችን እግዚአብሔር የጸጋ ሁሉ አምላክ መሆኑን ማወቅ ያጽናናናል። በማንኛውም ወጀብ እርሱን ታምነን መቆም እንድንችል እምነት ይሆነናል።

የዕብራውያን ጸሐፊም “እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ” (ዕብ. 4፥16) ብሎ ይናገራል። ስለሆነም በሚያስፈልገን ጊዜ ሁሉ ሊረዳን የሚችል ጸጋ እንደሚሰጠን፣ ከጸጋው አንዳች አንደማይጎድልብን አምነን እንቁም። አዎን በዚህ በወደቀው ዓለም ስለምንኖር፣ የወደቀም ሥጋ ስለ ተሸከምን ያለ ጸጋው መቆምም ሆነ መኖር አይቻልም።

ይህ ብቻም አይደለም፣ ጌታ አሁን የተቀመጠበት ዙፋን “የጸጋ ዙፋን” እንደሆነ ተገልጾአል። ቀሌምንጦስ ዘአሌክሳንደርያ የሚባል ከቤተ ክርስቲያን አባቶች አንዱ “እውነቱ ይህ ነው፦ ለሚያምኑና ለሚታዘዙ ሁሉ ማለቅያ የሌለውና የተትረፈረፈ ጸጋ ይበዛላቸዋል” ብሏል።  ስለሆነም ዛሬ ላሉበት ሁኔታ፣ ለሚያልፉበት ሁኔታና ተግዳሮት የሚያስፈልግዎትን ጸጋ ይቀበሉ ዘንድ በእምነት ወደ ጸጋው ዙፋን ይቅረቡ! ይህንም መዝሙር በጸሎት ሆነው ይዘምሩ!

ያለ ምህረትሕ ምን አለኝ

ያለ ይቅርታህ ምን አለኝ?

ምን አለኝ ጌታየ ሆይ፣ ምን አለኝ የሱሴ ሆይ . . .

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *