በእግዚአብሔር መታመን | ፓስተር ኤፍሬም ላእከማርያም

“በተከበበ ከተማ የሚያስደንቅ ምሕረቱን በእኔ የገለጠ እግዚአብሔር ይመስገን።
እኔስ ከዓይንህ ፊት ተጣልሁ፥ በድንጋጤ አልሁ፤ አንተ ግን ወደ አንተ በጮኽሁ ጊዜ የልመናዬን ቃል ሰማኸኝ” (መዝ. 31:21).

ይህ ቃል ዳዊት የዘመረው በጺቅላግ ተሸሽጎ ያሳለፈውንና እግዚአብሔር እንዴት እንዳስመለጠው በማሰብ ነው ይላሉ (1ዜና. 12:1)። ሌሎችም በቅዒላ በሳዖል ተከብቦ መውጫ መግቢያ ሁሉ ባጣበት ጊዜ እግዚአብሔር እንዴት እንዳስመለጠው በማሰብ የዘመረው ነው ይላሉ (1ሳሙ. 23)። ያም ሆነ ይህ እግዚአብሔር ምርጦቹን ከማንኛውም ከበባ እንደሚጠብቅና እንደሚያስመልጥ ይመሰክራል። አሁን ባለንበት ሁኔታም ዓለም ሁሉ በሞት ፍርሃት በተከበበት; መድሃኒት ያልተገኘለት ወረርሽኝ ሺዎችን እየቀሠፈ ባለበት ወቅት እግዚብሔር ለሕዝቡ የሚያስደንቅ ምሕረት ይገልጣል። ሕዝቡን ከክፉ ሁሉ የሚሸሽግበት የምሕረት ድንኳን አለው -“በመከራዬ ቀን በድንኳኑ ሰውሮኛልና፥ በድንኳኑም መሸሸጊያ ሸሽጎኛልና፥ በዓለት ላይ ከፍ ከፍ አድርጎኛልና” (መዝ.27:5)።

እኛንም እንዲሁ ይጠብቀናል። የተስፋ ቃሉን ይዘን በእምነት ጸንተን እንቁም፣ በጸሎት መትጋታችንን እንቀጥል።

እንግዲህ በእግዚአብሔር የምሕረት ድንኳን ውስጥ ሆነን ከዚህ በፊት በቀረቡት የጸሎት ርዕሶች መሠረት የጌታን ፊት እንፈልግ፣ ስለ ወገኖች ሁሉ፣ ስለ ዓለም ሕዝብ ሁሉ፣ የሥራ መስክ ድርጅቶች በመዘጋታቸው ምክንያት ከሥራ ለወጡት ሁሉ፣ በተለይ የካናዳ መኖሪያ ወረቀት የሌላቸውና በካሽ ሲሰሩ የቆዩት አሁን ግን መንግሥት የሚሰጠውን ድጎማ ለማግኘት እንኳ አድል የሌላቸው ስላሉ ስለ እነርሱ እግዚአብሔር ጣልቃ እንዲገባ፣ በተጨማሪም Front-line ሆነው እየተረባረቡ ስላሉና ለቫይረሱ በየቀኑ ስለሚጋለጡት የጤና ባለሙያዎችና ቤተሰቦቻቸው ጸሎት፣ ምልጃና ልመና ከእኛ እንዲቀርብ ጌታ ይጠብቃልና ሸክሙን ሁሉ ይዘን በፊቱ እንቅረብ። እነ አሮን ዕጣን ይዘው ሲያስተሠርዩ መቅሠፍት እንደተከለከለ አሁንም እንዲከለከል በጌታ ፊት የጸሎት ዕጣንን ይዘን መቃተታችንን እንቀጥል።

ማሳሰቢያ:- በቅርቡ በአዲስ መልክ በተደራጀው (በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሣሽነት) የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አማኞች ማህበር በመላ ኢትዮጵያ ከትናንት ጀምሮ የ7 ቀናት ጾም ጸሎት አውጇልና ከ20 ሚልዮን በላይ አማኞች አብረውን እንዳሉ በመንፈስ እያሰብን እንድንጸልይ አደራ።

“ጌታ እግዚአብሔር የዘላለም አምባ ነውና ለዘላለም በእግዚአብሔር ታመኑ” (ኢሳ.26:4)

ጌታ ይባርካችሁ!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *