ሁለት ሚልዮን የሚያህል ሕዝብ በውኃ ጥም ሲያጉረመርም መሪዎች ምን ማድረግ ይቻላሉ? ምንስ ማለት ይችላሉ? የምድረ በዳ ጉዞ እምነትን የሚፈትን ጉዞ ነው፣ አማኝ የሚናወጥበትና የሚበጠርበት ጉዞ ነው። ሰው በምድረ በዳ ሲያልፍ እንኳን በመሪዎች ላይ በእግዚአብሔር በራሱም ላይ እንኳ ብዙ መናገር የሚቃጣበት ወቅት ነው። አንዴ ይህ አማረኝ፣ አንዴም ያ አማረኝ እያሰኘ በመጎምጀት፥ ነገር ግን ባለ መርካት ጉዞ የሚደረግበት ሥፍራ – አስጨናቂ ጉዞ ያለበት!
“ለማኅበሩም ውኃ አልነበረም በሙሴና በአሮንም ላይ ተሰበሰቡ። ሕዝቡም ሙሴን ተጣሉት፥ እንዲህም ብለው ተናገሩት። ወንድሞቻችን በእግዚአብሔር ፊት በሞቱ ጊዜ እኛም ምነው በሞትን ኖሮ! እኛ ከብቶቻችንም በዚያ እንሞት ዘንድ የእግዚአብሔርን ጉባኤ ወደዚህ ምድረ በዳ ለምን አመጣችሁ? ወደዚህ ክፉ ስፍራ ታመጡን ዘንድ ከግብፅ ለምን አወጣችሁን? ዘርና በለስ ወይንም ሮማንም የሌለበት ስፍራ ነው የሚጠጣም ውኃ የለበትም። ሙሴና አሮንም ከጉባኤው ፊት ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ሂደው በግምባራቸው ወደቁ የእግዚአብሔርም ክብር ተገለጠላቸው” (ዘኁ. 20፥6)
ስለሆነም የእስራኤል ሕዝብ በዘኁልቍ 11 ላይ ሥጋ አማረን አሉ፣ ደግሞም በዚህ ክፍል ውኃ! ውኃ! ሲሉ ይደመጣል በምድረ በዳ ጉዞ! ሙሴና አሮንም እንዲህ ዓይነት ትርምስና ብጥብጥ ሲነሳ ሌላ ቦታ ሲናገሩ ይታያሉ። እዚህ ላይ ግን ምንም አላሉም፤ ዝም ብለው በእግዚአብሔር ፊት ብቻ ተደፉ። ጌታ ደግሞ ክብሩን ገለጸ፣ ተነሱና ለዓለቱ ተናገሩ አላቸው። አምላካዊው ምላሽም “ድንጋዩም ውኃን እንዲሰጥ እነርሱ ሲያዩ ተናገሩት! ከድንጋዩም ውኃ ታወጣላቸዋለህ እንዲሁም ማኅበሩን ከብቶቻቸውንም ታጠጣላቸዋለህ!” (ቍ.8) በማለት ተናገራቸው።
የከበደና ውስብስብ የሆነ ችግር ሲገጥመን የሚያዋጣን በእግዚአብሔር ፊት ተደፍተን እርሱን መለመን ብቻ እንደሆነ እንማራለን። እግዚአብሔርም ክብሩን ይገልጻል፣ የእግዚአብሔር ክብር ሲገለጥ ደግሞ ክድንጋይ ውኃን ማውጣት ይቻላል። ዳዊት ይህንን ጊዜ በመንፈስ በማስታወስ (መዝ. 78፥16) “ውኃን ከጭንጫ አወጣ፥ ውኃንም እንደ ወንዞች አፈሰሰ” ብሎ ይጠቅሰዋል። ሙሴም ከብዙ ጊዜ በኋላ “እባብና ጊንጥ ጥማትም ባለባት፥ ውኃም በሌለባት፥ በታላቂቱና በምታስፈራው ምድረ በዳ የመራህን፥ ከጭንጫ ድንጋይም ውኃን ያወጣልህን፣ በመጨረሻም ዘመን መልካም ያደርግልህ ዘንድ ሊፈትንህ ሊያዋርድህም አባቶችህ ያላወቁትን መና በምድረ በዳ ያበላህን አምላክህን እግዚአብሔርን እንዳትረሳ፤ በልብህም። ጉልበቴ የእጄም ብርታት ይህን ሀብት አመጣልኝ እንዳትል” (ዘዳ. 8፥15-16) ብሎ ያስጠነቅቃል።
ክብሩ እንዲገለጽ፣ ተአምራቱ እንዲታይና ለጥያቄ ሁሉ መልስ እንዲመጣ ሙሴ “ተናገር” ብቻ ነበር የተባለው። ነገር ግን መሴ ተሳስቶ “እጁን ዘርግቶ ድንጋዩን ሁለት ጊዜ በበትሩ መታው ብዙም ውኃ ወጣ፥ ማኅበሩም ከብቶቻቸውም ጠጡ” (ቍ. 11)። ምንም እንኳ ሙሴ ቢሳሳት፣ በመሳሳቱም የሚከፍለው ዋጋ ቢኖርም እንኳ እግዚአብሔር እንደ ተናገረ ከድንጋይ “ብዙ ውኃ ወጣ”፣ ውኃውም አላቋረጠም፤ ማኅበሩም ጠጡ! ረኩበት፣ በውሃም ተራጩበት።
ዛሬ ብዙ የምንጨነቅበት፣ ምንም መፍትሄ ልናገኝለት ያልቻልን ብዙ ውስብስብ ጥያቄ ሊኖር ይችላል። እስራኤል እንደተበጣበጡም ከችግር የተነሳ መበጣበጥ ሊኖር ይችላል። ችግር ሰውን ከሰው ጋር ያልትማል፣ ያጋጫል፤ ያጣላል፤ እርስ በርስ ያነካክሳል፤ ያውም ከጥላቻና ብጥብጥ በቀር ምንም ዓይነት መፍትሄ ላይገኝ፡
ዛሬም አሮንና ሙሴ ምንም ሳይናገሩ በማደርያው ድንኳን በእግዚአብሔር ፊት እንደተደፉ፣ እኛም ዝም ብለን ስለ ራሳችንም ሆነ ስለ ሌሎች ችግር በእግዚአብሔር ፊት ብንደፋ ጌታችን ክብሩን ይገልጻል፤ ጥማታችንን እርሱ ብቻ ያረካል። ለእኛ ብቻ አይደለም፤ በቤታችን ያሉ ሁሉንም የሚያረካ ምንጭ እግዚአብሔር ይከፍታል። ስለዚህ እስኪ ዝም ብለን በእግዚአብሔር ፊት እንውደቅ።
የውኃ ጥም ጊዜ የማይሰጥ ችግር ነው፤ አንተም አንቺም ያልጠበቃችሁትና ጊዜ የማይሰጥ ሌላ ዓይነት ችግር ደርሶባችሁ ግራ ተጋብታችሁ ይሆናል። እስኪ ወደ መገናኛ ድንኳን ውጡና በጌታ ፊት ተደፉ! የእግዚአብሔርን ክብር ታያላችሁ! በእንደዚህ ዓይነት ችግርም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ላይ የእግዚአብሔር ክብር እንዲገለጥልን ከእኛ ምን ይጠበቃል?
- እውነተኛ ንስሐ እንዲኖረን ያስፈልጋል።
- ያለ ምንም ማጕረምረም ችግሮቻችንን ሁሉን ቻይ ወደሆነው ጌታ ማቅረብ ይኖርብናል።
- መቀደስ ይኖርብናል፣
- ከሰው ጋር ተጋጭተን ከሆነ በይቅርታ መዝጋት ይኖርብናል፤
- እውነተኛ አምልኮ ለእግዚአብሔር መስጠት ይኖርብናል፣
- አንድ ልብ ልንሆን ያስፈልጋል።
- የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል በሚገባ መስበክ ይኖርብናል።