“አቤንኤዘር ” … | በፓስተር ዶ/ር ኤፍሬም ላእከማርያም

“አቤንኤዘር ” . . .እስከ አሁን ድረስ እግዚአብሔር ረድቶናል”

1 ሳሙ. 7፥12

“እቤን-ኤዘር” የሚለው ቃል “እስከዚህ ድረስ” ወይም “እስከ ዛሬ ድረስ ወይም “እስከ አሁን ድረስ” የሚል መንታ ትርጉም አለው። አንዱ ቦታን/ሥፍራን ሲያመለክት ሌላው ጊዜን ያመለክታል።

ታሪኩም እንዲህ ነው፦ እስራኤል በፍልስጥኤማውያን ላይ ድልን ከተቀዳጁ በኋላ ሳሙኤል አንድ ድንጋይ ወስዶ በምጽጳና በሼን መካከል እንዳኖረና ስሙንም “እቤንኤዘር” ብሎ እንደጠራው ተጽፎአል። ይህ ከመሆኑ ከሃያ ዓመታት በፊት ግን በእስራኤል “ኢካቦድ” ሆኖ ነበር – ማለትም፡ የእግዚአብሔር ክብር ከእስራኤል ለቅቆ መሄድ፣ የእግዚአብሔርም ታቦት መማረክና ብሎም የእስራኤል በጠላቶቻቸው ፊት መመታት አሳዛኝ የውድቀትና ሽንፈት ክስተት። ከሃያ ዓመት በኋላ ግን ሳሙኤል እስራኤልን ወደ ምጽጳ ሰበሰበና በጾምና በጸሎት፣ በንስሐም ሆነው በአምላካቸው ፊት እንዲቀርቡ አደረገ። ሳሙኤልም ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ። እግዚአብሔርም እስራኤል ወደ እርሱ እንደ ተመለሱ አይቶ ወደ እነርሱ ተመለሰ፣ ረዳቸው፣ ብሎም ፍልስጥኤማውያንን አሳልፎ ሰጣቸውና –ድል በድል ተጎናጸፉ። የውርደት ታሪክ በንስሐ ታደሰ፣ ከሃያ ዓመታት የቁዘማ ዘመን በኋላም በእስራኤል ካምፕ የድል ዝማሬ ሲዘመር ተሰማ። ይህንን ታላቅ የእግዚአብሔር የቸርነት ሥራ ወደፊት በሚመጣ ትውልድ እንዳይረሳ ለማድረግ ሳሙኤል ትልቅ ድንጋይ ተከለና በላዩ ላይ “አቤነኤዜር” ብሎ ጻፈበት። “እስከ ዛሬ ድረስ; እስከ አሁን ድረስ: እስከዚህ ድረስ እግዚአብሔር ረድቶናል!” ሲል!ይህም የእግዚአብሔር የታማኘነቱ፣ የእረኝነቱ፣ የረዳትነቱ፣ የአባትነቱ መዘክር ሆኖ ለትውልድ ይመሠክራል:: እያንዳንዳችንም እኮ ባለፍንባቸው አስቸጋሪ መንገዶች ሁሉ እግዚአብሔር ረድቶናል። ዛሬ በትዝታችን ማማ ላይ የቆሙ አያሌ የምሥክር ሃውልቶች እንዳሉን፣ በብዙዎቻችን ሕይወት ገና ያልተነገሩ የአምላካችን ድንቅ ሥራ ታሪኮች እንዳሉን አምናለሁኝ። ኧረ ስንቱን የማይታለፍ ሸካራ መንገድ አሳለፈን? ከሰላሳ-ሦስት ዓመታት በፊት በጅቡቲ በኩል በስደት፣ በብዙ መከራ ያለፈ አንድ ወዳጄ (ዛሬ አገልጋይ ነው) ከጅቡቲ ይዞት የመጣውን በትንሽ ፕላስቲክ የቋጠረውን አሸዋ አንድ ቀን አሳየኝ።እኔም ገርሞኝ ለምን? ብዬ ስጠይቀው “ከዚያ የመከራና የቃጠሎ ቦታ ያወጣኝን እግዚአብሔርን፣ ውለታውንም እንዳልረሳ ያስታውሰኛል። አሸዋው ለኔ የተአምራቱ ምልክት ሆኖልኛል፣ ያንን የነበርኩበትን የሞት ቀጠና እና እግዚአብሔር እንዴት ከዚያ በድንቅ ሁኔታ እንዳሻገረኝ እንዳልረሣ ይረዳኛል” አለኝ። ዋው! ተገረምኩ!ታድያ እግዚአብሔር እኮ የሁላችንም ባለውለታ ነው። ብናስተውለውም ባናስተውለውም “እስከዚህ ድረስ እግዚአብሔር ረድቶናል” እኮ! ለብዙ ዓመታት በመከራና በችግር፤ በከፍታና በዝቅታ፣ በሚመችም በማይመችም አሳልፎን ይኸው እዚህ ደርሰናል። በዚህ ሁሉም “እግዚአብሔር ረድቶናል” – አቤንኤዘራችን! ክብር ለስሙ ይሁን! አቤንኤዘር የሚለው ቃል ወደኋላ ብቻም ሳይሆን ወደፊትም የሚያመለክት ቃል ነው፡፡ ይህም ስንል እስከ አሁን ድረስ ታማኝ ሆኖ የረዳን ጌታ፣ ዛሬም ነገም እንደሚረዳን፣ እንደማይጥለን፣ ትናንት ያሻገረን ጌታ ዛሬም እንደሚያሻግረን ተስፋችንንና እምነታችንን የሚያድስ ቃል ነው። አሁንም በኮሮና ምክንያት ካለንበት አስጨናቂ ወቅት ያሻግረናል። ስለሆነም በምንም ሁኔታ ሳንጨነቅ በእምነት ጸንተን እንቁም!” ጴጥሮስ “እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት” ይላል (1ጴጥ. 5:7)። “ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና፣ ዛሬም እስከ ለዘላለምም ያው ነው!” (ዕብ. 13:8) አሜን!

እባክዎን “በሕይወቴ ጣልቃ እየገባ” የሚለውን የመስፍን ጉቱን መዝሙር እየዘመሩ የጌታን ውለታ እያስታወሱ ያመስግኑ። በተጨማሪም ይህን መዝሙር አዝማቹን እነሆ ጽፌዋለሁ፣ ቁጥሩን ይፈልጉና አብረን እንዘምር!

አቤንኤዘር የእግዚአብሔር እርዳታ

አቤንኤዘር ፈጥኖ ደርሶልናል

ከፊታችን ላለው ምንም ነገር

ትላንት ያደረገው ለዛሬ እምነት ሆኖልናል . . .

ጌታ ቀንዎን ይባርከው!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *