የጥሞና ቃል ክፍል 8

“ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል” ዮሐ. 16፥13

የመንፈስ ቅዱስ ምሪት፡- 

  1. የተለወጠ ሕይወት እንዲኖረን ያደርጋል፣ ማለትም የአሮጌው ሰው ባሕርያችንን (ዝሙት፣ ርኵሰት፣ መዳራት…) ከሕይወታችን እያስወገደ በመንፈስ ፍሬ ይተካዋል።
  2. ስለሆነም ኃጢአትን አሸንፈን በድል ሕይወት እንድንመላለስ ያደርገናል።
  3. በውስጣችን የእግዚአብሔር ፍቅር ስለሚፈስ የፍቅር ሕይወት እንዲኖረን፣ በፍቅርም እንድንመላለስ ያደርገናል።
  4. ለእግዚአብሔር የተሰጠ ሕይወት ማለትም የመታዘዝ ሕይወት እንዲኖረን ያደርገናል።
  5. ግራ ከመጋባት ያወጣናል፣ ስንደክም ያበረታናል፣ ስናዝንም ያጽናናል።
  6. ያስተምረናል፣ ወደ እውነት ሁሉ ይመራናል (ዮሐ. 14፣15, 26፤ 16፣12-15፤ 1ዮሐ. 2፣27፤ ሮሜ)

 

ነገር ግን አንዳንድ ሰዎች ጌታን ከተከተሉ ብዙ ዓመታት ቢሆንም ከዓለም ብዙም የተለዩበት ነገር ላይኖር ይችላል፤ አልፎ አልፎም ይህንን…ያንን…መተው አቃተኝ፣ ከኃጢአት መላቀቅ አቃተኝ፣ ምን ባደርግ ይሻልኛል? የሚሉ ይኖራሉ። መልሱም ባጭሩ በመንፈስ መሞላት ወይም በመንፈስ መመላለስ ነው።

ይህም ራስን ለጌታ ከመስጠት ጀምረን መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን እንዲሰራ መፍቀድ ይኖርብናል። በመንፈስ እንድንመላለስና በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወት እንዲኖረን ደግሞ በቅድስናና በንጽሕና መኖር ያስፈልገናል። ከሰዎች ጋር አብረን ለመኖር ማንነታችውንና ባሕርያቸውን ጠንቅቀን ማወቅ እንደሚኖርብን ሁሉ እንደዚሁም አማኞች ከሆንን በሕይወታችን ውስጥ የሚኖረውን መንፈስ ቅዱስን ማንነቱንና ባሕርዩን ከቃሉ እየመረመርን በነጻነት ነገር ግን በጥንቃቄ ልንመላለስ ያስፈልገናል (ኤፌሶን 4፣30)።

ለምሳሌ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ስለሆነ ከቅድስና ከሚያጎድለን አካሄድ ሁሉ ማለትም በአነጋገር፣ በአመለካከት፣ በአጠቃላይ በመንፈሳዊ ሕይወታችን፣ በባሕርያችንና በአኗኗራችን ላይ መጥፎ ዝንባሌና ተጽእኖ ከሚያመጡብን ዓለማዊ ጓደኞች ፈጽመን መለየት ይኖርብናል። ከመጥፎ ጓደኞች ሕብረት እንዳይኖረን ወስነን ካልተለየን ግን ሕይወታችን ፈጽሞ ሊቀየር አይችልም። ውሳኔ ማድረግና መለየት ካልቻልን ደግሞ እጅ ተጭኖ ቢጸለይ፣ ከኮንፍራንስ – ኮንፍራንስ ብንካፈል፣ ከቤተ ክርስቲያን ወደ ቤተ ክርስቲያን ብንዞር፣ ብዙ ብንጮህና ብናለቅስ ለውጥ አይመጣምእንዲያውም በአገራችን ምሳሌያዊ አነጋገር «ከአጋም ጋር የተጠጋች ቍልቋል እያለቀሰች ትኖራለች» እንደሚባለው፣ አማኞች እንደመሆናችን መጠን ከመንፈስ ቅዱስ የተነሣ በድል ሕይወት ልንመላለስ ሲገባን መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን ካልከበረ ወይም አኗኗራችን እርሱ የሚያዝንበት ከሆነ የሚኖረን ሕይወት ለውጥ የሌለው ሃይማኖት ብቻ፣ ኑሮአችንም የለቅሶ ኑሮ ብቻ ይሆናል።

እናስተውል! ከምንም ነገር ይልቅ በጌታ ያገኘነው አዲስ ሕይወት ይበልጥብናል። ቅዱስ ዳዊትም ይህን ስለሚያውቅ እንዲህ ብሎ ጸለየ፦

“ከፊትህ አትጣለኝ፣

ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድብኝ

የማዳንህን ደስታ ስጠኝ” መዝ. 50(51)፣11

ይህን ሲያነቡ ምን ተሰማዎት? የእርስዎስ ጸሎት ምን ይሆን? ለጌታ ያልተለዩበት፣ ከዓለም ጋርም የተመሳስሉበት፣ ለመንፈስ ቅዱስም ያልተመቹበት ክፍተት በኑሮዎና በአካሄድዎ ይኖር ይሆን? ለኃጢአትስ የተከፈተ ቀዳዳ በሕይወትዎ ይኖር ይሆን?

በዚህ ጽሑፍ ከተጻፈው መልዕክት በተጨማሪ ጌታ “ራቅ” ፤ “ተለይ” ያለባቸውን ክፍሎችና ሁኔታዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ፈልገው በማንበብ ሕይወትዎን ይመርምሩ! ሕይወትዎ “እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው፣ ቅዱስም መሥዋዕት” አድርገው እንዲያቀርቡ እንጸልይልዎታለን (ሮሜ 12፣1)።  የጸሎት እርዳታ ካስፈለግዎ ወይም ሊያገኙን ከፈለጉ በአድራሻችን ይደውሉልን ወይም ይጻፉልን!

ጌታ ይባርክዎ!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *