የዳዊት ጸሎት ለመንፈስ ቅዱስ ምሪት “ቅዱስ መንፈስህም በጽድቅ መንገድ ይምራኝ!” መዝ. (143፡10)
በዚሁ ክፍል ዳዊት የጸለየው የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማወቅ ብቻ ሳይሆን ለማድረግ ነው። እግዚአብሔር ፈቃዱን ለቅዱሳኑ ቢያንስ በሦስት ዋና ዋና መንገዶች ይገጻል። 1ኛ. በቃሉ፣ 2ኛ. በመንፈሱና 3ኛ. በሁነታዎች። ቅዱስ ዳዊትን ብቻ ሳይሆን እኛንም በከበረው የልጁ ደም የተዋጀን ልጆቹ ስለሆንን ዛሬም በመንፈሱ ይመራናል (ሮሜ 8)። ስለሆነም ፈቃዱን ለማወቅ ብቻ ሳይሆን ለማድረግ ወይም ለመታዝዝ እንደ ዳዊት ልንጸልይ ይገባል፣፡ መታዘዝ የሌለበት እውቀት ብቻውን ከንቱ ነው (ያዕ. 1፣22-25)። Vincent Aslop (1703) የተባሉ የእግዚአብሔር ሰው “እውቀት ያለ መታዘዝ አንካሳ ነው፣ መታዘዝ ያለ እውቀትም እዉር ነው፣ እውርንና አንካሳን ካቀረብን ደግሞ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት እናገኛለን ብለን ተስፋ ማድረግ ፈጽሞ የለብንም” ብሏል። የሁላችን ጥያቄም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ብናውቅም እንዴት መታዘዝ ይቻላል? ገና ያልተዋጀና የወደቀ ሥጋ የተሸከምን፣ በወደቀ ዓለምም የምንኖር ስለሆንን እንዴት በመታዘዝ ሕይወት መመላለስ እንችላለን? የሚል መሠረታዊ ጥያቄ ሊሆን ይችላል። ለዚሁ መልሱም በዚሁ ጥናታችን በ”ቅዱስ መንፈስህ…” የሚለው ቃል ነው። አዎን በራሳችን ኃይል ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ! በእርግጥ የእብራይስጡ ቃል የሚለው «ሩዋሓ ጦብ» “መልካሙ መንፈስህ” ነው። የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ብቻ ሳይሆን መልካምም ስለሆነ የመታዝዝ ሕይወት ይኖረን ዘንድ ኃይል ይሰጠናል፣ ያስተምረናል፣ ይመራናል። ስለሆነም ነህምያ “ያስተምራቸው ዘንድ መልካሙን መንፈስህን ሰጠሃቸው” (9፣20) ብሎ ይላል።
ያለ መንፈስ ቅዱስ ሰው ከንቱ ነው፣ ጠማማ መንገድንም ይከተላል፤ ያለ መንፈስ ቅዱስ ምሪት ሕይወት፣ ኑሮ፣ አገልግሎት ሁሉ ድካም ብቻ ይሆናል። ዳዊት ራሱ በቍ. 4 ላይ “ነፍሴ በውስጤ አለቀችብኝ” ሲል እንመለከታለን። እኛም እንደዚሁ ሕይወታችንንና አካሄዳችንን ለማስተካከል የመንፈስ ቅዱስ ጉልበትና ምሪት ያስፈልገናል።