“ለበረከትም ሁን! You Shall Be a Blessing!” ዘፍ. 12፣2
በ1998 ዓ.ም. ግንቦት ወር ውስጥ Rev. Ruddy Wiebe ከተባሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ኮሌጅ ፕሪንሲፓልና ሌሎች 6 ከተለያዩ አገሮች የመጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ጋር ፔንሲልቫንያና ኒውዮርክ ለአንድ ሳምንት በመዘዋወር በተለያዩ የአሜሪካ አብያተ ክርስቲያን የማገልገልና የመገልገል ዕድል ገጥሞን ነበር። በወቅቱ በተለያዩ ቦታዎች ብዙ አገልግለናል፣ ተባርከናልም። ወደ ቶሮንቶ ከመመለሳችን በፊት ግን አንድ ቀን የጉብኝትና የመዝናናት ቀን ተሰጥቶን ፔንሲልቫንያ ውስጥ ወደምትገኝ አንዲት ከተማ ተወሰድን። ከተማዋ ሄርሺ /Hershey/ ትባላላች። በዓለም የታወቀው የ Hershey KISSES ቸኮሌት የሚመረትባት ከተማ ነች። ከተማዋ የተቆረቆረችው ኋላም በስሙ እንድትጠራ የሆነው በአቶ Milton Hershey ነው።
አቶ ሚልተን መስከረም 13 ቀን 1857 ዓ.ም. ተወለደ። እናቱ ብርቱ አማኝ ክርስቲያን ስለነበረች በጸሎት፣ በጽኑ እምነትና ሥራዓት አሳድጋዋለች። አባቱ አቶ Henry Hershey ልጁ ሚልተን በአካዳሚ ጎበዝ እንዲሆንለት በመመኘት ጥሩ ት/ቤት አስገብቶት ነበር። ቤተሰቡ በየጊዜው ሥፍራ ይቀያይሩ ስለነበረ ግን ሚልተን በትምሕርቱ እየሰነፈ ሄደ። እንዲያውም እጅግ በመስነፉ ምክንያት ት/ቤቱን እንዲለቅ ተጠየቀና የ14 ዓመት ወጣት ሆኖ 4ኛ ክፍል ብቻ አጠናቅቆ ከት/ቤቱ ወጣ፤ ደደብ እየተባለም ሳይሳቅበት አልቀረም (1ኛ ኪሣራ)። በኋላም እናቱና አክስቱ ወ/ሮ Mattie ሚልተን በትምሕርት ዓለም እስክዚህም እንድማይሳካለት አባትየውን አሳመኑና ሚልተንን በአቅራቢያቸው በሚገኝ ቦታ በነበረው የማተሚያ ቤት በተለማማጅነት አስቀጠሩት። የማተሚያ ቤቱ ኃላፊ ግን ሚልተን በሚፈጽማቸው ተደጋጋሚ የግድ-የለሽ ስሕተቶች ትእግስታቸው አለቀና በቍጣ ፊታቸው አብጦ-ዓይናቸውም አጕረጥርጦ ወዲያውኑ ከሥራው አባረሩት (2ኛ ኪሣራ)።
እናቱና አክስቱ ግን እንደገና በከርሜላ ሥራ ፋብሪካ ውስጥ አስቀጠሩትና Royer’s Ice Cream Parlor & Garden በተባለ ካምፓኒ ከረሜላ እንዴት እንደሚሠራ በደንብ እየተከታትለ አራት ዓመት ሙሉ ሠራ። በኋላም በ1876 የ19 ዓመት ወጣት ሆኖ የራሱን ቢዚነስ ሥራ ለመክፈት ተዘጋጀ። በትልቅ ከተማ ውስጥ ቢሆን በቀላሉ እንደሚሳካለት በመተማመንም ወደ ፊላደልፊያ አመራ። በዚያም ከፍተኛ ጥረት አደረገ ነገር ግን ብዙ ወጪዎች እየተከመሩበት ከአቅሙ በላይ ዕዳ ውስጥ ተዘፈቀ፣ ቢዚንሱም ከሠረ (3ኛ ኪሣራ)።
ሚልተን ግን ፍጹም ተስፋ ሳይቆርጥ እንደገና ወደ ኮሎራዶ ተጓዘ፣ በዴንቨር ከተማ ለአንድ የጥሩ ከረሜላ አምራች ድርጅት ተቀጥሮ መስራት ጀመረ። በዚሁ ሥራ ሆኖ ትንሽ ፍራንክ አጠራቀመና ወደ ኒው ዮርክ መጥቶ የከረሜላ ሱቅ ከፈተ። ነገር ግን በሚያሳዝን ሁኔታ አሁንም ቢዚነሱ ከሠረ (4ኛ ኪሣራ)።
ከዚያም ትልቅ የተስፋ መቍረጥ ጥቁር-ደመና በላዩ ላይ እያንዣበበት ወደ ላንካስተር (ፔንሲልቫንያ) ከተማ መጣና ተቀመጠ። ከዚያ በፊት በገንዘብ የረዳው አጎቱም ይህንን የከረሜላና ጣፋጭ ነገር ቢዚንስ ሥራ ተስፋ የሌለውና ለሚልተን የሚሆን ነገር እንዳልሆነ አስረድቶ ከዚሁ ዓላማው ሊያስቆመው ሞከረ። ሚልተን ግን ተስፋ ለመቍረጥና በልቡ ያለውን ራዕይ ለመተው ፈቃደኛ አልሆነም፣ ዘራፍ! እጄን አልሰጥም አለ።
በኋላም Herry Lebkicher ከሚባል ሌላ ወዳጁ በተደረገለት እርዳታ አማካይነት እንደገና ዕቅዱን ጀመረ፣ በዚህ ጊዜ ግን በአንዲት ምርት ላይ ብቻ አተኮረ፣ ከረሜላን ማምረት! ከዚያም በአጭር ጊዜ ውስጥ የLancaster Caramel Company በከተማይቱ ውስጥ በጣም ከታወቁ ሱቆች አንዱ ለመሆን በቃ። በ1900 ዓ.ም. ግን ይህንን ካምፓኒ ለአንድ ሚልዮን ዶላር ሸጠው። ይህ ገንዘብ በወቅቱ ፈርጠም ያለ ሃብት ነበር። ምናልባት ይህ ገንዘብ በሌሎች እጅ ቢሆን ኖሮ ወዲያው ጡረታ ይወጡና ይንደላቀቁበት ነበር።
ሚልተን ግን Cornfield በምትባል ባደገባት ገጠር አጠገብ ያለች መንደር ትልቅ የቸኮሌት ፋብሪካን ለማቋቋም በማሰብ ከባድ የፋብሪካ መሣሪያዎችን በመግዛት ገንዘቡን አንቀሳቀሰ። በዚህ ምንም በሌለበትና ገጠር-ቢጤ በሆነ ቦታ ይህንን ማሰብና ይህን ሁሉ ገንዘብ የሚጨርስ ፋብሪካ አቋቍማለሁ ማለቱ ለብዙዎች የቡና-ጨዋታ፣ መሳቂያና-መሳለቂያ ሆኖ ነበር።
ሠራተኞችስ የት ያገኛል? ለፋብሪካው የሚያስፈልጉ ጥሬ-ዕቃዎችና የተመረቱም ነገሮች እንዴት ሊያጓጓዝ ነው? እያሉ በጠባብ አመለካከት ይሳለቁበት ነበር። ሚልተን ግን ምንም አልተበገረም። መልስ ነበረውና፦ የትም ላለመሄድ፣ ነገር ግን በዚያው በአከባቢው ከተማን ለመቈርቈር መወሰኑ!
ቢዚነሱ እያደገ በሄደ ቍጥርም የተመሠረተው ከተማ እያደገ ሄደ። በኋላም በዓለም ትልቁ የቸኮሌት ማምረቻ ፋብሪካ ሆነ። በተለይ በ1930ዎቹ የታላቁ መደበት (Great Depression) ጊዜ ብዙ ካምፓኒዎችና ፋብሪካዎች ሲከስሩና ሲዘጉ፤ በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ የሰሜን አሜሪካ ሰዎችም ሥራ-አጥ በሆኑበት ዘመን የሚልተን ቸኮሌት ፋብሪካ በብዙ ሺ የሚቆጠሩትን ሰዎች በመቅጠር የብዙ ቤተሰብን ነፍስ ታደገ። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የምዕራቡ ዓለም ወታደሮች ወደ ልዩ ልዩ ቦታዎች ሲላኩ የሚልተን ዘመናዊ ምርት፣ ችኮሌትን ይዘው እየሄዱ አሊያም እየተላከላቸው ስለነበር በአጭር ጊዜ ውስጥ በዓለም ዙርያ አስተዋወቁት። በዚህ ሁኔታ ኪስስ-ሀርሺ ቸኮሌት በመላዋ ዓለም ታዋቂና ተፈላጊ ሆነ፣ ዛሬ ሕጻን ልጅ ገና ከእናቱ ማህጸን ሲወጣ ቸኮሌት አለ ቢባል አያስደንቅም።
ሚልተን ለራሱ፣ ለካምፓኒው ማናጀሮችና ሠራተኞች መኖሪያ ቤቶችን አሠራ። ቀስ በቀስ ት/ቤት፣ ሆስፒታል፣ ሆቴሎችን፣ ማሰልጠኛ አዳራሾችን፣ መዝናኛና የሽርሽር ቦታዎችን፣ የሕጻናት መዋያና የእንክብካቤ ቦታዎችን እያሠራ እያስፋፋም ሄደ። ምንም የሌላት መንደር ብቻ የነበረችው ዛሬ በአንድ የበረከት ሰው አማካይነት ትልቅ ከተማ ሆነች። ስሟም በራሱ ስም ተሰይማ Hershey ተባለች። Hershey ዛሬ ትልቅ የቱሪስት መስህብ ነች። የቸኮሌት ፋብሪካው ውስጥ ብቻ የኮክና ሌላ የቅባት ፍሬዎች፣ ከማርና ከወተት እያደባልቁ ልዩ ልዩ ዓይነቶች ቸኮሌቶችን ሥራ በየደረጃው እንዴት እንደሚሠሩ እየተዘዋወሩ ለማየት ቢያንስ ሁለት ሰዓት ይጠይቃል።
በተጨማሪም የከተማዋ አየርና ንፋስ በቸኮሌት መዓዛ የተሞላ ነው። የመንገዶችዋ የመብራት አምፑሎችም በ KISS Hershey ቅርጽ የተሰሩና የሚያሸበርቁ ናቸው።
በሕይወቱ አራት ትልልቅ የኪሣራ ጊዜዎችን ቢያሳልፍም ለተስፋ መቍረጥና ለውድቀት እጄን አልሰጥም ብሎ በጸናውና አምላኩን በመተማመን በቆመው ሚልተን ይህ ሁሉ በረከት ተገኘ፣ አዎን ሚልተን ለትውልድ የሚተርፍ የበረከት ሰው ሆነ! በዕድሜው መጨረሻ ላይ ከባለቤቱ ጋር ሆነው አባትና እናት የሌላቸውን ብዙ ሺ የሚቆጠሩ እጓለ-ማውታ ሕጻናትን ለማሳደግና ለማስተማር ት/ቤቶችን ሰሩ። ሃብታቸውንም በአብዛኛው ለዚህ ቅዱስ ስራ እንዲሆን ተናዝዘዋል።
- የእምነት አባታችን አብርሃምስ?
ስንት ጊዜ ተፈተነ? ስንትስ ጊዜ ሕይወቱ ለተስፋ መቍረጥና ብሎም ለውድቀት ተጋለጠ? እርሱ ግን በአምላኩ በመታመን የጸና ሰው በመሆኑ በእምነቱ ተመሰከረለት። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚነግረንም፦
“ለሙታን ሕይወት በሚሰጥ፣ የሌለውን እንዳለ አድርጎ በሚጠራ ባመነበት በአምላክ
ፊት የሁላችን አባት ነው…የብዙ አህዛብ አባት እንዲሆን ተስፋን ይዞ አመነ” ሮሜ 4፣17
ጌታ ለአብርሃም የገባውን ቃል ፈጸመ፣ አብርሃም እንደጌታው ቃል ለበረከት ሆነ! አንተስ? አንቺስ? በዙርያችሁ በምታዩት ነገር ተስፋ አትቍረጡ! የእግዚአብሔር ዓላማ ሁላችን በክርስቶስ ኢየሱስ ለበረከት እንድንሆን ነው። ስለሆነም ጌታን ተደግፋችሁ ቍሙ! ጽኑ! ለበረከትም ትሆናላችሁ!
ጌታ አብዝቶ ይባርካችሁ!