የጥሞና ቃል ክፍል 11

 “እግዚአብሔርን በመተማመን የሚጠባበቁ ግን ኃይላቸውን ያድሳሉ

እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ ይሮጣሉ፥ አይታክቱም ይሄዳሉ፥ አይደክሙም”

(ኢሳ. 40፥31) (ከቍ. 23 – 31 ያለውን አንብብ)

ሰይጣን ሰዎችን ለማጥቃት ከሚጠቀምባቸው መሣርያዎች አንዱ ተስፋ ማስቆረጥ ነው። ተስፋ ስንቆርጥ ጸልየንም ሆነ ጮኸን እግዚአብሔር የሚሰማን አይመስለንም። እንባቆም ባካባቢው ከነበረው ሥርዓት አልባነትና ቀውስ የተነሣ ተስፋ ቆርጦ ነበርና “አቤቱ፥ እኔ ስጮኽ የማትሰማው እስከ መቼ ነው? ስለ ግፍ ወደ አንተ እጮኻለሁ፥ አንተም አታድንም” (ዕንባ. 1፥2) እያለ ያንጎራጕር ነበር። ዳዊትም “አምላኬ፥ አምላኬ፥ ለምን ተውኸኝ? እኔን ከማዳንና ከጩኸቴ ቃል ሩቅ ነህ” (መዝ. 22፥1) እያለ የጮኸበት ጊዜ ነበር። ካህኑ ዘካርያስ ልጅ አልነበረውምና ብዙ ጠብቆ ተስፋ በመቍረጥ ደረጃ ላይ ነበር። ነገር ግን አንድ ቀን መልአኩ ገብርኤል “ዘካርያስ ሆይ፥ ጸሎትህ ተሰምቶልሃልና አትፍራ ሚስትህ ኤልሳቤጥም ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፥ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ፤ ደስታና ተድላም ይሆንልሃል፥ በመወለዱም ብዙዎች ደስ ይላቸዋል” ብሎ ሲያበስረው አምኖ ለመቀበል ተቸገረ። “እኔ ሽማግሌ ነኝ፣ ሚስቴም በዕድሜዋ አርጅታለችና ይህን በምን አውቃለሁ?” ሲል በጥርጣሬ ጠየቀ። ዘካርያስ አገልጋይ ካህን ነበር፣ ቢያንስ ስለ አብርሃምና ሣራ ማርጀትና ነገር ግን በእግዚአብሔር ኃይል ይስሐቅን መውለድ ያውቃል፣ ለሌሎችም ሰብኮት ይሆናል። ሰው በራሱም ሆነ በሁኔታዎች ተስፋ ከቆረጠ እንኳን ሌላ ሰው አይዞህ ብሎት እግዚአብሔር ራሱ ቢያናግረው እንኳ ለማመን ይቸገራል። እርስዎስ?

ከተስፋ መቍረጥ የተነሳ በውስጣችን “ለኔ አይሆንልኝም” የሚል ስሜት ስለሚሰማን እግዚአብሔር ሲናገር እንኳ ሊያስቀን ይችል ይሆናል። ሳራ በልብዋ ሳቀች (ዘፍ. 18፥13-15) ተብሎ እንደተጻፈው። አልአዛር ከሞተ በኋላ ኢየሱስ ማርታን “ወንድምሽ ይነሳል” ሲላት “በመጨረሻ ቀን በትንሣኤ እንዲነሳ አውቃለሁ” አለች፣ በትንሽ እውቅውትዋ ከጌታ ጋር የምትከራከር ይመስል። ተስፋ ስንቆርጥ ትእግስታችን ያልቃልና ከእግዚአብሔር ጋር እንኳ ክርክር ገጥመን ሊሆን ይችላል።

የሚያስፈልገን ጥቂት መታገስና ጌታን መጠበቅ ነው፤ ጌታን ሳንጠብቅ ደግሞ ምንም የምናገኘው ነገር አይኖርም። መጠበቅ ሲያቅት አልሆነ ውሳኔ ላይ የመውደቅ ፈተና አለ። እስራኤል ብዙ ተአምራትን የተለማመዱና የእግዚአብሔርን ክብር ያዩ ሕዝብ ነበሩ፤ ነገር ግን ሙሴን መጠበቅ አቃቷቸው ጣዖትን ሰርተው ለማምለክ የራሳቸው አማራጭ ውሳኔ አደረጉ (ዘጸ. 32፥1-6)። ብዙ ጠብቀን ተስፋ ስንቆርጥ የራሳችን ውሳኔ የማድረግ ፈተና ይገጥመናል። እግዚአብሔርን በመጠባበቅ የሚቆዩት ራሳቸውን ሲያድሱ በራሳቸው ውሳኔ የሚሄዱት ግን በብዙ ኪሳራ ላይ ይወድቃሉ። ሁሉ ነገር ይዘበራረቅባቸዋል።

ዛሬ ተስፋ የቆረጡበት ጉዳይ ይኖር ይሆን? ብዙ ጠብቀው ትዕግስትዎ ያለቀበት ጉዳይ አለ? “ቢዘገይም በእርግጥ ይመጣልና ታገሠው፣ እርሱ አይዘገይም” ይላልና አሁንም ጌታን በመተማመንና በትእግስት ይጠብቁ። እየጠበቁት ዓመታት ቢቆጠሩም እንኳ “በእርግጥ ይመጣል!”ተብሏልና ታግሰው ይጸልዩ! ይጠብቁም! መልካም ቀን!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *