የጥሞና ቃል ክፍል 12

ከሰጢም ተነሱ፣ ዮርዳኖስን ተሻገሩ፣ ተስፋውን ውረሱ” (ኢያሱ 3)

            እስራኤል ዮርዳኖስን ሳይሻገሩ በሰጢም ብዙ ጊዜ ቆይተዋል። በቆይታቸው ጊዜም ብዙ ነገር ደርሶባቸዋል። ለምሳሌ ከሌሎች ጋር ተደባለቁ፣ የሌሎችን ባህል በመሃከላቸው አስገቡ፤ ተስፋቸውን ጣሉ (ተዉ)፣ ብዙ ኀሳረ-መከራን አዩ። እኛም ዛሬ እንዲሁ፣ ተስፋችን አርጅቶ፣ የመከራ ጊዜአችንም ረዝሞ ሊሆን ይችላል። እግዚአብሔር ግን የገባውን ተስፋ ይፈጽማል እንዲሁ አይጥልም። የመከራ ጊዜአችን ረጅም ቢሆንም የመፍትሄው ጊዜ ግን በእግዚአብሔር ዘንድ አጭርና ጥቂት ነው። እግዚአብሔር በሂደት ብቻ ሳይሆን በድንገትም ብዙ ታላላቅ ነገሮችን ይሠራልና ስለሆነም ሕይወታችንን ሆነ ሁኔታችንን ድንገት ይለውጣል።  ብዙ ጊዜ በሕይወታችን ማታ ለቅሶ መጥቶ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን በዚያው ባለቀስንበት ማታ ሌሊት ምን እንደተሠራ ሳናውቀው ማለዳ ደስታ ይሆንልናል “እነሆ ክረምት አለፈ፣ የዜማም ጊዜ ደረሰ” የሚል የምስራች እንሰማለን። ዛሬ ብናለቅስ ለቅሶን በደስታ የሚለውጥ አምላክ ከእኛ ጋር አለ። ዳዊት “ክብሬ ትዘምርልህ ዘንድ ዝምም እንዳትል ልቅሶዬን ለደስታ ለወጥህልኝ፥ማቄን ቀድደህ ደስታንም አስታጠቅኸኝ” (መዝ. 30፥11)፤ “በማለዳ ምሕረትህን እንጠግባለን በዘመናችን ሁሉ ደስ ይለናል ሐሤትም እናደርጋለን” (መዝ. 90፥14)። “ቍጣው ለጥቂት ጊዜ ነው፥ ሞገሱ ግን ለሕይወት ዘመን ልቅሶ ማታ ይመጣል፥ ጥዋት ግን ደስታ ይሆናል!” (መዝ. 30፥5)። እስኪ በዚህ ቀን ካሉበት ይነሡ! ከተያዙበት ሁኔታ ይውጡ! እግዚአብሔር ወዳሰበልዎት ይሻገሩ! እግዚአብሔር ያየልዎትን ለመውረስ ይዘጋጁ!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *