“ኢያሱም ካህናቱን፦ የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸክማችሁ በሕዝቡ ፊት እለፉ ብሎ ተናገራቸው
የቃል ኪዳኑንም ታቦት ተሸክመው በሕዝቡ ፊት አለፉ” (ኢያሱ 3፥6)
እስራኤል ዮርዳኖስን ለመሻገር ታቦቱን ማስቀደም ነበረባቸው። እግዚአብሔር ይህንን ትዕዛዝ ለካህናቱ የሰጠውም ታቦቱ የእግዚአብሔር አብሮነት ተምሳሌት ስለ ነበር ነው። ሌላው ታቦቱ ከፊት እንዲመራቸው የሆነው ሃሳባቸው፣ ትኵረታቸውና አመለካከታቸው ወደ አምላካቸው እንዲሆን ነበር። ታቦቱን መከተልም በአዲስ መንገድ የመሄድ ምሳሌ ነበር፡ ወደ አዲስ መንገድ፣ ወደ አዲስ አሠራር፣ ወደ እግዚአብሔር ምሪት መግባታቸውንም የሚያሳይ ነው። ጌታን ስንከተለው ይመራናል፣ ያሻግረናልም። ዳዊት “ለዓለምና ለዘላለም ይህ አምላካችን ነው፥ እርሱም ለዘላለም ይመራናል”(መዝ. 48፥14) ይላል።
ምናልባት ጌታን ቀድመነው ከሆነ ወይ ዘግይተን ኋላ ቀርተን ከሆነ ዛሬ ወደ ኋላ ተመልሰን አካሄዳችንን ማስተካከል ይኖርብናል። እኛ የጌታን ምሪት ስንከተል በእኛና በጌታ መካከል ሃሳባችንንና ትኵረታችንን የሚሠርቅ፣ እይታችንን የሚጋርድ ሌላ ነገር መኖር የለበትም። አካሄዳችንን መመርመርና በጥንቃቄም መከተል ይኖርብናል።
ጌታን ስንከተለው አላሻግር የሚል የዮርዳኖስ ሙላት በፊታችን ሊታየን ይችላል፤ አንዳንዴም መንገዱ ለሌላ ሰው አስፋልት ሲሆን ለእኛ ግን ኰረኮንች ሊሆን ይችላል። ዛሬ የእኛ ሕይወት ከፍታና ዝቅታ የሚቆጣጠሩ ሰዎች ወይም ሥራችን ወይም የተለያየ ነገርም አይደለም፤ ነገር ግን በላይ ያለው፣ ሁሉን ቻይ የሆነው እግዚአብሔር ነውና በእምነት እንከተል! ዮርዳኖስም ተከፍሎ እንሻገራለን!