“ጴጥሮስም ሁሉን ወደ ውጭ አስወጥቶ ተንበርክኮም ጸለየ፥ ወደ ሬሳውም ዘወር ብሎ። ጣቢታ ሆይ፥ ተነሺ አላት።
እርስዋም ዓይኖችዋን ከፈተች ጴጥሮስንም ባየች ጊዜ ተቀመጠች። እጁንም ለእርስዋ ሰጥቶ አስነሣት፤
ቅዱሳንንና መበለቶችንም ጠራ ሕያውም ሆና በፊታቸው አቆማት” (ሐ.ሥ. 9፥40-41)
ዛሬ የሞተብህ ነገር አለ? የሞተብሽ ነገር ምንድነው? ምንም መፍቲሄ ሊሰጡ ከማይችሉ ሰዎች ተቀምጠህ ሬሳን እያየህ ይሆናል። ሬሳን በፊትህ አኑረህ እያለቀስህ ይሆናል። የምስራች! ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ጴጥሮስ ሲጸልይ ጣቢታን አስነስቷታል ከሞት! ጣቢታን እንዳነሳት ዛሬ ጣቢታህን/ሽን ሊያስነሳ ይቻለዋል። ነገር ግን ጣቢታ እንድትነሣ የሞተብህ/ብሽ ነገር እንዲነሳ ጴጥሮስ ያደረገውን ማድረግ ያስፈልጋል። 1. ሁሉን ወደ ውጭ አስወጣ 2. ሁሉን በሚችል በእግዚአብሔር ፊት ተንበረከከ 3. ጸለየ. 4. የእምነት ቃል ተናገረ፡- ጣቢታ ሆይ ተነሺ!
የሞተ ነገር በፊትህ ተጋድሞ ይሆናል፣ ከማዘንህም የተነሳ ልብህ ተሰብሮ ይሆናል። ሬሳው የተለያየ ችግር ወይም አልነቃነቅ ያለ ተራራ ሊሆን ይችላል። ከተራራው የተነሣ ምን እንዳተርግ ግራ ገብቶህ፣ ልብህም በጭንቀት፣ በጥርጥርና በፍርሃት ተሞልቶ ይሆናል። አሁን ልብህን ያጣበቡ ሌሎች ነገሮችን ወደ ውጭ አስወጣ! በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ተንበርክከህ ጸልይ። ለችግርህ፣ ለተራራህ፣ ሬሳ ለሆነብህና ለሞተብህ ተስፋ በእምነት ሆነህ በኢየሱስ ስም ቃሉን ተናገር! የሞተብህ ተስፋ ሕያው ሆኖ በፊትህ ይቆማል፤ እግዚአብሔር ተአምራትን ያደርጋል! ሁሉን ቻይ ኤልሻዳይ ነውና!
“ወደ እኔ ጩኽ፥ እኔም እመልስልሃለሁ አንተም የማታውቀውን ታላቅና ኃይለኛ ነገርን አሳይሃለሁ” ኤር. 33፥3