የሚጠራችሁ የታመነ ነው፣ እርሱም ያደርገዋል!” ( 1ተሰ. 5፥24)
ጌታ በብዙ ነገር ለኛ ታማኝ ሆኖ ይኸው እስከዛሬ ቆመናል። ከእግዚአብሔር ጋር የተራመዱ ታላላቅ የእግዚአብሔር ባርያዎችም ይህ ታማኝነቱ እጅግ እያስገረማቸውና እያስደነቃቸው አልፈዋል። የእግዚአብሔር ባርያ ሙሴ ባሕርያተ እግዚአብሔርን እንዲህ በማለት ይገልጸዋል!
“እርሱ አምላክ ነው፣ ሥራውም ፍጹም ነው
መንገዱም ሁሉ የቀና ነው፣
የታመነ አምላክ ክፋትም የሌለበት፣
እርሱ እውነተኛና ቅን ነው” (ዘዳ. 32፥4)”
ጌታ ይቅርታ በማድረግ የታመነ ነው፣ “በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው” (1ዮሐ. 1፥9)። ጌታ በቃሉ የታመነ ነው፣ “ቃሉ የታመነ ነው እንዲህ የሚለው፣ ከእርሱ ጋር ከሞትን፥ ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንኖራለን (2ጢሞ. 2፥13)፤ “የተስፋ ቃል የሰጠው እርሱ የታመነ ነው” (ዕብ. 10፥19-23) “በዙፋንም የተቀመጠው። እነሆ፥ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ አለ፣ ለእኔም እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸውና ጻፍ አለኝ” (ራዕ 21፥5)።
ዛሬም ጌታ ለአርስዎ የታመነ ነው፣ ይህንን አይርሱ። ለሰጠዎት ቃል የታመነ ነው፤ ለሰጠዎት ቤተሰብ የታመነ ነው፤ ለሰጠዎት አገልግሎት የታመነ ነው፤ ለሰጠዎት ጸጋ የታመነ ነው። ስለሆነም አሁን ይነሱና የጌታን ታማኝነት እያሰቡ የምስጋናን መሥዋዕት ይሠዉ! ቤተሰብ አንድ ላይ ሆናችሁ የእግዚአብሔርን ታማኝነት ባያችሁበት ነገር ሁሉ አመስግኑት! ሃሌ ሉያ!