“ኤርምያስ ገና በግዞት ቤት አደባባይ ታስሮ ሳለ የእግዚአብሔር ቃል ሁለተኛ ጊዜ እንዲህ ሲል መጣለት። ስሙ እግዚአብሔር የሆነ፥ ያደረገው እግዚአብሔር፥ ያጸናውም ዘንድ የሠራው እግዚአብሔር እንዲህ ይላል።
ወደ እኔ ጩኽ፥ እኔም እመልስልሃለሁ አንተም የማታውቀውን ታላቅና ኃይለኛ ነገርን አሳይሃለሁ” (ኤር. 33፥1-3)
በመጀመሪያ ኤርምያስ በምን ሁኔታ እንደነበረ በክፍሉ የተጠቀሰውን ማስተዋል ይኖርብናል። “በግዞት ቤት አደባባይ ታስሮ” እንደነበር እንመለከታለን። በዚያ በግዞት እስር ቤት ሳለ ቃሉ ለሁለተኛ ጊዜ እንደመጣለት ተጠቅሷል። ይህም ቀደም ብሎም የእግዚአብሔር ቃል መጥቶለት ነበር ማለት ነው። እንዴት ሁለተኛ? የመጀመሪያውን ሳይሰማ ወይም ሳያስተውል ቀርቶ ይሆን? እንዴት ሊያልፈው ቻለ? ይህንን ጥያቄ የሚመልስ በክፍሉ የተጻፈ ነገር ባይኖርም ከሰው የሕይወት ገጠመኝ ልምምድ በመነሳት ያለበት ሁኔታ የእግዚአብሔርን ድምጽ በጊዜው እንዳይሰማ ተጽእኖ አሳድሮበት ይሆናል የሚል እሳቤ ያሳድራል። ወይስ ቃሉ አሁን ያለበትን ሁኔታ የሚገልጥ ወይም ካለበት ሁኔታ የሚያወጣ ፈጣን መልስ ሲጠብቅ ቆይቶ ይሆን?
አንዳንዴ የምናልፍበት ሁኔታና እግዚአብሔር የሚናገረን ቃል ለጊዜው የማይገጣጠም መስሎ ሊታየን ይችላል። ጌዴዎን ከምድያማውያን ለመሸሸግ በወይን መጥመቂያው ውስጥ ስንዴ እየወቃ ሳለ የእግዚብሔር መልአክ ለእርሱ ተገልጦ “አንተ ጽኑዕ ኃያል ሰው፥ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው አለው”። ይህ ቃል ለጌዴዎን ዱብ ዕዳ ነበር፣ ውጫዊ እውነታው በፍርሃት ተሸሽጎ ስንዴ እየወቃ ያለበት ጊዜ ነበር። በስሜቱ የተረዳውና ያለበት ሁኔታም የሚገልጠው ፈሪነቱንና በሚያስፈራ ሁኔታ መገኘቱን ነበርና ከመልአኩ የሰማውን ቃል ማመን አቃጠው። እንዲያውም ጥያቄ ሆኖበት “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ነገር ሁሉ ለምን ደረሰብን? አባቶቻችንስ እግዚአብሔር ከግብፅ አውጥቶናል ብለው ይነግሩን የነበረ ተአምራቱ ወዴት አለ? ወዴት አለ? አሁን ግን እግዚአብሔር ትቶናል፥ በምድያማውያንም እጅ አሳልፎ ሰጥቶናል አለው” (መሳ. 6፥12-13)።
የነበረበት ሁኔታ እግዚአብሔር ከርሱ ጋር እንዳለ የሚያረጋግጥለት ሆኖ አላገኘውም ነበርና “እግዚአብሔር ትቶናል” ወደሚል የተስፋ መቍረጥ ድምዳሜ ደረሰ። እግዚአብሔር ሕያው ሆኖ ሳለ ጌዴዎን ግን ከሚያልፍበት ሁኔታ የተነሣ የእግዚአብሔር ነገር በሕያውነቱ ሳይሆን በታሪክነቱ ብቻ ነበር የተረዳው። ስለዚህም “ተአምራቱ ወዴት አለ?” ለማለት ደረሰ። የዚሁ ተስፋ መቍረጥ መረዳቱ ማጠቃለያ ሀሳቡም “እግዚአብሔር ትቶናል”፤ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ቢሆን ኖሮ ይህ ባልደረሰብንም ነበር የሚል ነበር።
ዛሬስ ስንቶቻችን እንሆን በተመሳሳይ ሁኔታ የምንገኝ? የምናልፍበት ሁኔታና እግዚአብሔር የሚናገረው አልጋጠም ብሎን የመጣልንን ትንቢታዊ ቃል ለመቀበል ያቃተን ስንቶች ነን? በእርግጥ ሁኔታዎች ሲከብዱ እንኳን ሰው የእግዚአብሔር መልአክ (ጌታ ኢየሱስ ራሱ) ቢናገረን እንኳ ለመስማትና ለማመን የሚያስቸግረን ሊሆን ይችላል። እግዚአብሔር ግን በፊት አልሰማህምና ብሎ ኤርምያስን አልተወውም፣ የእንደገና አምላክ ነውና ቃሉን “ሁለተና ጊዜ” ላከለት። ለሁሉተኛ ጊዜ በተላከው ቃልም እግዚአብሔር ራሱ ስሙን በመግለጽ ጀመረ። ስሙ አምላካዊ ባሕርዩን፣ መለኮታዊ ማንነቱን፣ ሕያውነቱንና ቅዱስ ሥራውን ይገልጻል። በክፍሉ የተጻፈው ስሙም በእብራይስጥ ቋንቋ “ያህዌ” የሚለው ቃል ነው። ይህም የቃል ኪዳን አምላክና ሕያው መሆኑን ይገልጻል። ቀጥሎም ሉዓላዊነቱን፣ ሁሉን ማድረግ የሚቻለው፣ የሚሠራ፣ የሚያጸና፣ በሥልጣን መናገር የሚችል፣ የተናገረውንና የፈቀደውን ማድረግና መፈጸም የሚችል አምላክ መሆኑን፣ ከሁኔታዎች በላይ መሆኑን ገልጾ “ወደ እኔ ጩህ!” አለው። ማን መሆኔን በማወቅ “ወደ እኔ ጩህ” እያለው ነው።
ኤርምያስ ተስፋ ከመቁረጡ የተነሳ መጸለይ እንኳ አቅቶት ኖሮ ይሆን? በዚህም ሆነ በዚያ ጌታ “ወደ እኔ ጩህ” አለው። እኛም ዛሬ ወደ ጌታ እንጩህ! ወደ ‘ጻድቃን’፣ ወደ መላእክት፣ ወደ ቀሳውስት፣ ወደ ሙታንም ሆነ ወደ ሕያዋን፣ በአጥቃላይ ወደ ሥጋ ለባሽ ሰዎችም ሆነ ወደ መናፍስት ብንጮህ ለውጥ ልናመጣ አንችልም። ሁሉም በጊዜና በቦታ የተወሰኑ ፍጡራን ስለሆኑ ምንም ሊያደርጉልን አይችሉም። እግዚአብሔር ግን ሁሉን የሚችል፣ ሁሉን የሚያውቅ፣ ሁሉ በሁሉ ያለ፣ ስፍራና ጊዜ የማይወስነው፣ ኪዳኑን የሚጠብቅ፣ ሕያውና የቃል ኪዳን አምላክ ስለሆነ ወደ እርሱ እንጩህ።
ዛሬ እርስዎ በምን ሁኔታ እንዳሉ አላውቅም፤ ኤርምያስን ግን “ገና በግዞት ቤት አደባባይ ታስሮ ሳለ” ሁሉን ቻይ እግዚአብሔር “ወደ እኔ ጩህ” አለው። ስለዚህ እኛም እንዲሁ ወደ እግዚአብሔር እንጩህ! ካለንበት ሁኔታ፣ በተስፋ መቍረጥ ግዞትም ሆነን ቢሆን፣ በሕመም፣ በእሥራትና በተለያዩ ተግዳሮቶች ውስጥ እንኳ ብንሆን አምላካችን ታሪክ አይደለም ዛሬም ሕያው ነው። ሕያው ስለሆነ ታሪክን ይለውጣል! እንባን ያብሳል! አምላካችን ከሁኔታዎች በላይ ነው፣ በከንቱም “ወደ እኔ ጩህ!” አላለምና ይህ ጊዜ ወደ እርሱ የምንጮህበት ሰዓት ይሁን!
“በመከራ ቀን ጥራኝ፥ አድንህማለሁ አንተም ታከብረኛለህ!” (መዝ. 50፥15)።