“እስኪምረን ድረስ. . . .”
መዝ. 123፥2
“እነሆ፥ የባሪያዎች ዓይኖች ወደ ጌታቸው እጅ እንደ ሆኑ፥ የባሪያይቱም ዓይን ወደ እመቤትዋ እጅ እንደ ሆነ፥ እንዲሁ እስኪምረን ድረስ ዓይናችን ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ነው”
2ዜና 20፥12
“አምላካችን ሆይ. . . . ይህን የመጣብንን ታላቅ ወገን እንቃወም ዘንድ አንችልም፤ የምናደርገውንም አናውቅም፤ ነገር ግን ዓይኖቻችን ወደ አንተ ናቸው”
የተወደዳችሁ የኢ. ወ. ቤተ ክርስቲያን ምዕመናንና አገልጋዮች!
የመጀመሪያውን የሰባት ቀናት ጾምና ጸሎት በዛሬው ዕለት ጨርሰን ሁለተኛውን የሰባት ቀን ጾምና ጸሎት ከነገ ሰኞ April 6 ጀምሮ እንቀጥላለን፡፡ የኮቪድ-19 ቫይረስ መቅሰፍት እየቀጠለ፣ በሺዎች የሚቆጠሩትንም እየቀጠፈ ባለበት በዚህ ሰዓት በእግዚአብሔር ፊት መትጋታችንን እንቀጥላለን፡፡
ስለሆነም የጤና እክል ካላቸው በቀር ሁላችንም ከሰኞ ጀምሮ በአምላካችን ፊት በንስሐ ራሳችንን እናዋርድና፣ የአምላካችንን ፊት እንፈልግ ዘንድ መጾምና መጸለያችንን እንድንቀጥል ቤተ ክርስቲያን አውጃለች፡፡ ለዚሁም በያለንበት ቤት ሆነን እየጾምን ማታ ማታ ደግሞ ከ9pm – 11pm በተከፈተው የቤተ ክርስቲያን የጸሎት መስመር እየገባን እንድንጸልይ አደራ እንላለን፡፡
የጸሎት ርዕሶች፦
- እያንዳንዳችን ስለራሳችን፣ ስለቤተሰቦቻችን፣ ስለ ጉባኤያችን፣ ስለ ከተማችን፣ ስለ አገራችንና ስለ ዓለም ሕዝብ ሁሉ ንስሐና ምልጃ፣
- በዮናስ ዘመን “ቀኛቸውንና ግራቸውን የማይለዩ ከመቶ ሀያ ሺህ የሚበልጡ ሰዎች ላሉባት ለታላቂቱ ከተማ አላዝንምን?” ያለው አምላክ ለሕዝቡ እንዲራራ፣ ምሕረቱንም እንዲያወርድ፣
- እግዚአብሔር ሕዝቡን፣ ኪዳኑንና ቃሉን እንዲያስብ፣
- የኮቪድ ቫይረስ መቅሰፍት እንዲከለከል፣
- ቤተ ክርስቲያናችንንና አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ጌታ እንዲያስባቸው፣
- በቀውሱ ምክንያት ከሥራ የወጡት ሁሉ ወደ ሥራ እንዲመለሱ፣ አዳዲስ የሥራ በሮችም እንዲከፈቱ፣
- በየሆስፒታሉ Front-line ላይ እየተዋደቁ ላሉት የጤና ባለሙያዎች ሁሉ፣ ልዩ የእግዚአብሔር ጥበቃ በላያቸው እንዲሆን፣
- በዚህ ቀውስ ውስጥ ብዙዎች ወንጌል ሰምተው እንዲድኑ፣ የጠፉትም እንዲመለሱ፣
- እግዚአብሔር ክብሩን እንዲገልጽና “በመጨረሻው ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ” ብሎ በሰጠው ተስፋ መሠረት ሪቫይባል በዓለም ዙርያ እንዲነሣሳ:
“በስሜ የተጠሩት ሕዝቤ ሰውነታቸውን አዋርደው ቢጸልዩ፥ ፊቴንም ቢፈልጉ፥ ከክፉ መንገዳቸውም ቢመለሱ፥ በሰማይ ሆኜ እሰማለሁ፥ ኃጢአታቸውንም ይቅር እላለሁ፥ ምድራቸውንም እፈውሳለሁ”
2ዜና 7፥14
“እንግዲህ እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ ጸጥና ዝግ ብለን እንድንኖር፥ ልመናና ጸሎት ምልጃም ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ”
1ጢሞ. 2፥1-2